Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

Author: Yonas Habesha

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ::

(ሰኔ 26/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች፣ የንብረት ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም የተሸከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ሥራ አስፈጻሚዎች እን ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በኢ-ፍሊት (e-Fleet Management System) ትግበራ እና በመንግስት ንብረት አወጋገድ አፈጻጸም ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

 

በመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የውይይት መድረኩ በሀገራችን የመንግስት ንብረትና የተሸከርካሪ አስተዳደር ሥርዓትን የበለጠ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂ እና ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው የለውጥ ጉዞ ውስጥ አንዱ አስፈላጊ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል። ዋና ዳይሪክተሯ አያይዘውም የንብረት አያያዝና አወጋገድ ስርዓቱም ከባቢን በማይበክል እና መልሶ መጠቀምን በሚያበረታታ መልኩ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

የንብረት አያያዝንና አወጋገድን አፈጻጸምን አስመልክቶ ገላጻ ያቀረቡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያ እና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላክ ተጓዴ በበኩላቸው የመንግስት ተቋማት ያሉባቸውን የአፈጻጸም ክፍተቶች መለየት ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ አገልግሎት የማይሰጡና የተከማቹ ንብረቶችን በተገቢው ሒደትና ፍጥነት ማስወገድ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲሁም የንብረት አያያዝንና አወጋገድን ለማሻሻል እየተወሰዱ ስላሉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን አብራርተዋል።

አቶ መላኩ በማብራሪያቸው አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች በወቅቱ ካልተወገዱ የማከማቻ ወጪ እንደሚያስከትሉ፣ የንብረት መዝገቦችን እንደሚያዛቡ፣ የሥራ ቦታዎችን እንደሚያጨናንቁ እና የሙስና ተጋላጭነትን የሚጨምሩ በመሆናቸው በሕግና በመመሪያዎች መሠረት መፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

በሌላ በኩል የኢ-ፍሊት (e-Fleet) ሥርዓት አጠቃቀምንና ተያያዥ አፈጻጸሞችን በተመለከተ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP Project) ማናጀር አቶ ያፌት መኮንን ዝርዝር ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ሥርዓቱ በመንግስት ተሸከርካሪዎች አስተዳደር ውስጥ ግልጽነትን ለማሳደግ፣ ወጪን ለመቆጣጠር እና ውሳኔዎችን በመረጃ ላይ ተመስርተው እንዲወሰኑ ለማድረግ የተዘረጋ መሆኑ ተገልጿል።

ከቀረቡት ገለጻዎች በኋላ ከተሳታፊ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ለቀረቡት ጥያቂዎችና አስተያየቶች የማጠቃለያ ማብራሪያ የሰጡት የመንግስት ሀብት የህዝብ ሀብት በመሆኑ በአግባቡ መጠቀምና መጠበቅ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን በቀጣይም ተቋማቱ የኢ-ፍሊት ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ፣ መረጃዎችን ወቅታዊ እንዲያደርጉ፣ የንብረት አወጋገድ ሂደቶችን በወቅቱ እንዲያስፈጽሙ እና የአመራር ክትትልን እንዲያጠናክሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በዚሁም ተጠያቂና ዘመናዊ የንብረት አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ በመደረስ ውይይቱ በስኬት ተጠናቋል።

 በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ታትሞ ከተሰራጨው የኦዲት ተግባራት የተቀነጨበ

ጥያቄ፡ የኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ሥርዓት ምንድን ነው? ለምንስ አስፈለገ?

አቶ አዲስ:- የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (Electronic Government Procurement/ e-GP) ማለት ሁሉንም የመንግሥት ግዥ ሂደቶች በኤሌክትሮኒክ መንገድ የሚያከናውን የቴክኖሎጂ ሥርዓት ነው። ይህም ማለት የግዥ ሂደቱ ከግዥ ዕቅድ ዝግጅት ጀምሮ የጨረታ ማስታወቂያ፣ የተጫራቾች ምዝገባ፣ የጨረታ ግምገማ፣ የውል አስተዳደር እና ሪፖርት አያያዝ ድረስ ዲጂታል በሆነ መንገድ በአንድ ማዕከላዊ ሥርዓት ውስጥ ይከናወናሉ።

ዲጂታል ሥርዓቱ ያስፈለገው የወረቀት ሥርዓት ለጊዜ መጓተት፣ ለመረጃ መጥፋት፣ ለሙስና ተጋላጭነት እና ለውሳኔ አሰጣጥ አለመግለጽ ምክንያት ስለሚሆን ነው። የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ይህንን በመቀየር የግዥ ሥርዓቱን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ አድርጎታል። ሌላው ጉዳይ ሀገራችን ዲጂታል ኢኮኖሚን በቁርጠኝነት እየተገበረች

 የምትገኝ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናን ከቴክኖሎጂ ጋር አጣምራ በትኩረት እየሠራች እንደሆነ ይታወቃል። ስለሆነም የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) የሀገራችን ዲጂታል ኢኮኖሚ በማገዝ ረገድ ያለው ሚና የጎላ ነው።

ጥያቄ፡ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት (e-GP System) ከሕጋዊነት ኦዲት ጋር እንዴት ይገናኛል?

አቶ አዲስ:- የሕጋዊነት ኦዲት ዋና ዓላማ የግዥ ሂደቶች ከሕግ እና ከመመሪያ ጋር ተጣጥመው መፈጸማቸውን ማረጋገጥ ነው። በዚህ ረገድ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት (e-GP System) ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትን እና ቅልጥፍናን በማረጋገጥ ከሕጋዊነት ኦዲት (Compliance Audit) ጋር በቀጥታ ይገናኛል።

የኦዲት አካላት እንደ አዋጅ፣ መመሪያ እና ደንቦች ያሉ የግዥ ሕጎች መከበራቸውን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ትክክለኛ መረጃዎችን፣ የግብይት ሰነዶችን እና የውሳኔ ዱካዎችን (Audit Trails) ከሲስተሙ በቀላሉ ማግኘት ያስችላል። በመሆኑም ኦዲተሮች የጨረታ ማስታወቂያ መቼ እንደወጣ፣ ስንት ተጫራቾች እንደተሳተፉ፣ የግምገማ ሂደቱ እንዴት እንደተከናወነ እና ውሳኔው በምን መስፈርት እንደተሰጠ ወጪን፣ ጊዜና ጉልበትን ሳያባክኑ ባሉበት ሆነው በቀላሉ ማረጋገጥ ይችላሉ። ይህም የኦዲትን ሥራ የበለጠ ቀላል፣ ተዓማኒ እና ትክክለኛ ያደርገዋል።

 የመንግሥትኤሌክትሮኒክግዥሥርዓትግልፀኝነትንበመፍጠርየሙስናተጋላጭነትንይቀንሳል›› – አቶ አዲስ ጎዳና

የኢፌዴሪ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የተሰጡትን ኃላፊነትና ተግባር ለማከናወን እያደረገ የሚገኘውን እንቅስቃሴ በዚህ ዓምድ ላይ በማቅረብ አንባቢዎች ስለ ባለሥልጣኑ ግንዛቤ እንዲኖራቸው እየተደረገ ይገኛል፡፡

በዚህ መሰረት በባለፈው ዕትም ስለ ዘላቂ የመንግሥት ግዥ ምንነት፣ ዓላማዎች፣ መርሆዎች፣ አተገባበር እና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ምን መደረግ እንዳለበት በመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ከሆኑት ከአቶ ዮናስ ሀበሻ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ አቅርበን ማስነበባችን የሚታወስ ነው፡፡

በዛሬው ዓምዳችን ደግሞ የኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ሥርዓት የሕጋዊነት ኦዲት እና የኦዲት ክትትል ሚናን በሚመለከት ከክዋኔና ሕጋዊነት ኦዲት ክትትል ሥራ ክፍል መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አዲስ ጎዳና ጋር ቆይታ በማድረግ ምላሻቸውን ይዘን ቀርበናል፡፡

በቅድሚያ የክዋኔና ሕጋዊነት ኦዲት ክትትል ሥራ ክፍልን ተልዕኮ እና ኃላፊነት ቢያብራሩልን ?

አቶ አዲስ:- ጥያቄውን ከመመለሴ በፊት መነሻ ማድረግ የሚያስፈልገው ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 13 ምን ይላል የሚለውን ማየት አስፈላጊ ይሆናል። በዚህ አዋጅ አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 13 የመንግሥት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር እንዲሁም የመንግሥት እና የግል አጋርነት ዘርፍ ግዥዎችን አፈፃፀም በራሱ ዕቅድ፣ እንዲሁም ጥፋት ስለመፈፀሙ ጥቆማ ሲቀርብለት ሂደቱን በማስቆም የሥርዓት መጠበቅ ወይም የክዋኔ ኦዲትና ክትትል የማካሄድ እና በግኝቱ መሠረት ተገቢውን ርምጃ እንደ አግባብነቱ በራሱ መውሰድ ወይም ሥልጣን ባላቸው ሌሎች አካላት እንዲወሰድ ማድረግ መሆኑን ያስቀምጣል።

ይህን መነሻ አድርገን የክፍሉን ሥራ ስንመለከት የክዋኔና ሕጋዊነት ኦዲት ክትትል ሥራ ክፍል በመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የሚፈጸሙ ተግባራት ከሕግ፣ ከደንብ፣ ከመመሪያ እና ከተቀመጡ አሠራሮች ጋር ተጣጥመው መፈጸማቸውን ለማረጋገጥ የሚሠራ ክፍል ነው።

በተጨማሪም የኦዲት ግኝቶችና ምክረ ሀሳቦች በተገልጋይ ተቋማት ተግባራዊ መደረጋቸውን በመከታተል የአሠራር ክፍተቶች እንዲታረሙ እና የተቋማት የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት እንዲጠናከር ያግዛል። በመሆኑም ክፍላችን በመንግሥት ግዥ ሥርዓት ውስጥ የተጠያቂነትና የግልፅነት ባሕል እንዲጎለብት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ

(ሰኔ 18/2018 ዓ/ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የንብረት ማስወገድ ሂደት እና የኢፍሊት ማናጅመንት (e-Fleet Management) አተገባበርን በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።

የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በንግግራቸው የመንግስት ሀብትና ንብረትን በቁጠባ፣ በግልጽነትና በብቃት ማስተዳደር ያለውን የላቀ ጠቀሜታ ያብራሩ ሲሆን የተሽከርካሪ ስምሪትና ነዳጅ አጠቃቀም ስርዓትንም በጥብቅ ስነ- ምግባር መተግበር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

የንብረት አያያዝና አወጋገድን በሚመለከት ገለጻ ያቀረቡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያ እና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላክ ተጓዴ በበኩላቸው የመንግስት ተቋማት ያሉባቸውን የአፈጻጸም ክፍተቶች መለየት ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ አገልግሎት የማይሰጡና የተከማቹ ንብረቶችን በተገቢው ሒደትና ፍጥነት ማስወገድ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ  እንዲሁም የንብረት አያያዝንና አወጋገድን ለማሻሻል እየተወሰዱ ስላሉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የተሽከርካሪ ስምሪት እና ነዳጅ አጠቃቀም ስርዓትን (e-Fleet management Sysytem) አፈጻጸምና አሁናዊ ሁኒታን በሚመለከት የኢጂፒ (e-GP) ፕሮጀክት ጽ/ቤት ማናጀር አቶ ያፌት መኮንን ገለጻ ቀርቧል። አቶ ያፌት በገለጻቸው በፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ላይ ያለው የኢፍሊት ማናጅመንት አፈጻጸም ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲሁም ስርዓቱ የመንግስት ተሽከርካሪዎችን ቁጥጥር ለማዘመን፣ የነዳጅና የጥገና ወጪን ለመቀነስ ብሎም ግልጽነትን ለማስፈን እያበረከተ ስላለው አስተዋጽኦ እና ስርዓቱ ያለበትን የትግበራ ደረጃና በቀጣይ ሊሻሻሉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በእለቱ የሙስና ተጋላጭነት ስጋት ጥናትም በስነ- ምግባርና ጸረ- ሙስና ኮሚሽን ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የቀረቡትን ገለጻዎች መነሻ በማድረግ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል። በመጨረሻም በክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ  እና ባለደረቦቻቸው የጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የእለቱ ውይይት ተጠናቋል።