ባለስልጣኑ የስልጠና አሰጣጥን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመ።
(ሰኔ 09/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥና ንብረት ፕሮፌሽናላይዜሽን ስልጠናን ከፍ ለማድረግ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። የመግባቢያ ስምምነቱ የግዥና ንብረት አስተዳደር የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ፕሮግራምን በጋራ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ ሲሆን የግዥና ንብረት ባልሙያዎችን በስነ- ምግባር የታነጹ እንዲሁም ሁለንተናዊ አቅምን፣ ሙያዊ ብቃትን እና አፈፃፀምን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።
በፊርማ ስነ- ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት ስምምነቱ በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን እና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መካከል የተመሰረተ የስትራቴጂክ ትብብር ምልክት ሲሆን በኢትዮጵያ የመንግሰት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ስርዓት ላይ ብቃት ያለው ባለሙያ ለማፍራት የተደረገ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን አመላክተዋል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም የትብብር ስምምነቱ ዋና ዓላማ ባለሙያዎችን ማብቃትና ማሻሻል፣ የግዥ ሕጎችን በትክክል ማስፈጸም የሚችሉ ባለሙያዎች ማፍራት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት እና ብቃት ያለው የሀብት አጠቃቀም ማሳደግ፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተደራጀ የስልጠና ስርዓት ማቋቋም መሆናቸውን አብራርተዋል።
ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ የግንኙነትና የስራ ሰንሰለቱን ሲያብራሩ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ፕሮግራሙ ላይ የፖሊሲ አቅጣጫ መስጠት፣ የስልጠና ይዘት ማዘጋጀት፣ ሰልጣኞችን እና አሠልጣኞችን መምረጥ፣ የግምገማ ሂደት መምራት እና ሰርተፊኬት መስጠትን በሚመለከት በከፍተኛ ሀላፊነት የሚሰራ ሲሆን አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ እንደ ዋና የአካዳሚክ ተቋም የስልጠናውን ዕለታዊ አስተዳደር፣ የመማሪያ አካባቢ አቅርቦት፣ የሠልጣኝ ሁኔታ ክትትል እና በሁሉም ሂደቶች ባለስልጣኑን በማማከር በኩል በከፍተኛ ትጋት ሀላፊነቱን እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ደረጄ (ዶ.ር) በበኩላቸው ስምምነቱን እውን የሚያደርጉ ስራዎች አስቀድሞ ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተው ስምምነቱ ሁለንተናዊ ብቃትን የተላበሰ የግዥና ንብረት ባለሙያ ለመፍጠር እንደሚያግዝ አብራርተዋል።






