የባለሥልጣኑ ኃላፊዎች መልእክት

የዋና ዳይሬክተሯ መልዕክት
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በሁሉም ግዥ ፈጻሚ የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች፣ የልማት ድርጅቶች በመንግሥት ግዥ አፈፃፀም እና ንብረት አወጋገድ ረገድ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም በመገንባት፣ የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አስተዳደር ውጤታማ በሆነ መንገድ የሚፈጸም ስለመሆኑ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ፣ በጥናት ላይ በመመርኮዝ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ አሰራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና የአሰራር ማነቆዎችን ለመቅረፍ የሚያስችል ግልጽ፣ ቀልጣፋ፣ ፍትሐዊና ተጠያቂነት የተረጋገጠበት የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደርን ለማስፈን እየሰራ ይገኛል፡፡ባለስልጣኑ የህግ፣ የአሰራር እና የአደረጃጀት ማሻሻያ በማድረግ የሰው ሀይል አቅም በመገንባት እና አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ሥርዓትና ቁጥጥርን በማጠናከር የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም እንዲያስገኝ ለማስቻል እንዲሁም አፈጻጸሙ በአለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው መስፈርቶች ሲመዘን ውጤታማነቱ በሚፈለገው ደረጃ እንዲሆን የባለስልጣኑን አገልግሎትና አስተዳደር የማሻሻያ ስራዎችንም እየሰራ ይገኛል፡፡በመሆኑም በዘርፉ የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና የአሰራር ማነቆዎችን ለማስወገድ በየበጀት ዓመቱ ለመንግስት ግዥ የሚመደበው ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ንዋይ ተመጣጣኝ የሆነ ፋይዳ እንዲያስገኝ እና በከፍተኛ ወጪ የተገዛው ንብረት ከብክነት በጸዳ መንገድ ሥራ ላይ የሚውልበትን የአሰራር ሥርዓት በማጠናከር ለሀገራዊ ሁለተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ለማበርከት ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡በመሆኑም ለዚህ እቅድ መሳካት ሥራዎችን ህግና አሠራርን መሠረት በማድረግ በቅንጅትና በትብብር መስራት ወሳኝ በመሆኑ ባለስልጣኑ የሚመለከታቸው የመንግስትና የግል ባለድርሻ አካላት በተለይ የሁሉም ግዥ ፈጻሚ የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች እና የልማት ድርጅቶች አመራርና ፈጻሚዎች ዘርፉ በላቀ ደረጃ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቀባችሁን ሚና እንድትወጡ ጥሪዬን እያስተላለፍኩ በባላስልጣኑ በኩል ለሰመረ የስራ ግንኙነትና ለውጤታማነት ያለሰለሰ ጥረት እንደሚደረግ ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር

የምክትል ዋና ዳይሬክተሩ መልዕክት
ኢትዮጵያ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በዲጂታል ኢኮኖሚ መስፋፋትና በብዝሃ ዘርፍ ልማት በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ መድረክ ትኩረት የምትስብ ሀገር እየሆነች መጥታለች፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይም የዓለም ባንክ(WB)፣ አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እና የአውሮፓ ህብረት(EU) ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለውጥ እውቅና እየሰጡ ሲሆን፤ ዘላቂ ሁለተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈበበት ብቁ የመንግሥት ግዥና ሥርዓት ቁልፍ ሚና እንዳለው ይታመናል፡፡ በዚህ ወሳኝ ወቅት የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት በሕጋዊ ማዕቀፍ እና በዘመናዊ አሰራር መታገዙ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልጽግናችን መሰረታዊ መደላድል ይፈጥራል፡፡ የመንግሥት ግዥ አፈጻጸምና ንብረት አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት አመታዊ በጀት ከፍተኛውን ድርሻ እንደመያዙ፤ በተለይም በኢትዮጵያ ልማት ፖሊሲ ውስጥ እንደ መሠረተ ልማት፣ ትምህርት፣ ጤናና ግብርና ባሉ ዘርፎች የሚደረገው ወጪ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። ይህንን ሀብት ያለብክነት፣ በግልጽነትና በብቃት ሥራ ላይ ማዋሉን የሚረጋግጥ ብቁ ሥርዓት መዘርጋት ለኢትዮጵያ ብልጽግና ዋስትና ይሆናል፡፡
በዚሁ ሀገራዊ ርዕይ መሰረት የተሻሻለው የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016፤ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን (እንደ UNCITRAL Model Law on Public Procurement፣ WTO Government Procurement Agreement መሰረታዊ መርሆች) ከኢትዮጵያ ልዩ ሁኔታ ጋር ያጣጣመ ነው፡፡ ዋና ዓላማውም ሕጋዊ ማዕቀፎችንና አሰራሮቻችንን በማዘመን ግልጽ፣ ፍትሐዊ፣ ውድድር፣ ውጤታማና ተጠያቂነት የሰፈነበት የግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት ማጎልበት ነው፤ ይኸውም በመንግሥት ወጪ የሚደረግ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ብልጽግና ከፍተኛ ፋይዳ (Value for Money) እንዲያስገኝ የማረጋገጥ ተልኮን አንግቧል፡፡
ተልዕኮውን ከግብ ለማደረስ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርአቱን ከተበታተነ ባህላዊና አሰራር በማላቀቅ ከፍተኛ ብቃት ወዳለው ዘመናዊ ሥርአት ማሸጋገር ይጠይቃል፡፡ ለዚህም የሕግ ማዕቀፍችን ከማሻሻል ባሻገር፤ አስፈላጊውን ሰብዕዊና ዘመናዊ አቅሞ ከዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ጋር በተናበበ በፈጠራና ፍጥነት በመገንባት፣ ሕጋዊ ማዕቀፎቻች በጥብቅ ሥነ-ምግባርና ቅልጥፍና በመተግበር ወደር የሌለው ኢኮኖሚያዊ አዋጪነትን ማረጋጋጥ የሚያስችል ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ በአጭር ጊዜ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን(e-GP) በሁሉም የፌደራል ተቋሟት ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ተግባራዊ በማድረግ፤ እንዲሁም በቀሩት ክልልሎችና የመንግስት ልማት ድርጅቶች ተግባራዊ ለማድረግ የዝግጅት ምዕራፍችን በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የዲጂታል ኢትዮጵያ አንድ አካል የሆነ የኤሌክትሮንክ ግዥ ሥርአት አንዱ የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ አካል ሲሆን ከሁሉም የመንግስት ዲጂታል አገልግሎቶች ጋር የተናበበ ቀልጣፋ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ተደራሽ የአገልግሎት አሰጣጥን በማስቻል የታለመለትን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ በተጨባጭ ማረጋገጥ አስችሏል፡፡
አዋጁ ከአሥራር ሥርዓት ዝመና ባሻገር ለበርካታ ልዩ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በቀዳሚነት ምቹና ፍትሐዊ የውድድር ሜዳ በመፍጠር በግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ የሆነውን የአገር ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ ማነቃቃትና ተወዳዳሪ ገበያ ማበረታታት ሲሆን፣ ይህም የዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባል ለመሆን በወሰንበት ወቅት ፍትሐዊ ውድድር ማረጋገጥ መሠረታዊ መስፈርት በመሆኑ ከዓለም አቀፍ ንግድ ሥርዓት ጋር የተጣጣመ ያደርገዋል፡፡ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚመረቱ ምርቶች፣ ለአገር ውስጥ ተቋራጮችና አማካሪዎች፣ ለታዳጊ ኢንተርፕራይዞችና ለቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ልዩ ማበረታቻ (Preference Margins) በመስጠት ተወዳዳሪነት አቅማቸውን ያጎለብታል፡፡ ሲለጥቅ አዋጁ ዘላቂ ግዥና የንብረት አስተዳደር ሥርዓትን (Sustainable Procurement) ያበረታታል፤ ይኸውም በግዥ አፈጻጸም የሕይወት ዘመን ወጪ ትንተና (Life Cycle Cost Analysis) እንዲካተት በማድረግ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን (Recycling) በማበረታታት ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ አሰራሮችን በማበረታታት የመንግሥት ወጪ ከአካባቢ ጎጂ ተጽዕኖ በጉልህ በመቀነስ፤ ከዓለም አቀፉ ዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) በተለይም ከግብ 12 (ኃላፊነት የሚሰማው ፍጆታ እና ምርት) ጋር በማጣጣም ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ በአጠቃላይ አዋጁ ሙስናን በመከላከል፣ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሩዊን፣ ዕሴት የተከለበት ምርትን፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራን በማበረታታት ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጥቅም ያስገኛል፡፡
ከዚህ አንፃር የላቀ የሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ጽኑ አጋርነት እጅጉኑ ወሳኝ ነው፤ በተለይም መንግሥታዊ ተቋማት ሕጉን በዘመነ አሰራር በትጋትና ብቃት መተግበር፣ የግሉ ዘርፍ በሕጋዊ አግባብ በሥነ ምግባር በመወዳደር፣ ሲቪል ማህበረሰብ እና ሚዲያ ገንቢ ክትትል በማድረግ ግልጽነትን ማረጋገጥ፣ እንዲሁም ዜጎች የሚከፍሉት ግብር ምን ላይ እንደሚውል መጠየቅ እና ማወቅ ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ መላው የፌዴራል ተቋማት፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ተወካዮች፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና ዜጎች ለዚህ ሀገራዊ ራዕይ ስኬት ከባለስልጣኑ መሥሪያ ቤት ጋር በትብብርና በቅንጅት በመደመር እሳቤ እንድንሰራ በታላቅ አክብሮት ለመጋበዝ እወዳለሁ።
ምኒልክ ሣሙኤል
የባለስልጣኑ ም/ ዋና ዳይሬክተር