በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ንብረቶች አያያዝ፣ አጠባበቅ እና አወጋገድ ስርዓት- ለአካባቢ ደህንነትና ለህዝብ ጤና አዲስ ምዕራፍ

በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016 አንቀጽ 12 ንዑስ አንቀጽ 22 ላይ ለኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል አንዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በጤና ወይም በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ጊዜያቸው ያለፈባቸው አደገኛ ኬሚካሎች ወይም የኬሚካል ውጤቶች፣ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች፣ መድኃኒቶች፣ ጨረራ አመንጪ ዕቃዎች፣ የኢንዱስትሪ ዝቃጮችና የግብርና ተረፈ ምርቶች አያያዝና አጠባበቅ፣ እንዲሁም አወጋገድ ላይ ጥናት በማከናወን የአሠራር ሥርዓት እንዲዘረጋ ማድረግ መሆኑ ተደንግጓል።
ስለሆነም ይህን ተግባሩን እውን ለማድረግ ባለስልጣኑ የፌዴራል መንግስት ተቋማት በጤናና በአካባቢ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ንብረቶች አያያዝ፣ አጠባበቅ እና አወጋገድ ላይ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ጥናት እንዲጠና አድርጓል፡፡ ጥናቱን እና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችን መሰረት በማድረግ የአፈጻጸም ማንዋል አዘጋጅቷል።
ባለሥልጣኑ ያዘጋጀው ማንዋል በጥልቀት ሲቃኝ ምን ይመስላል የሚለውን ሀሳብ መነሻ በማድረግ ከባለስልጣኑ የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያ እና አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ተጓዴ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡
በጤናና በአካባቢ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ንብረቶች አያያዝ፣ አጠባበቅ እና አወጋገድ ችግር ምን ያህል አሳሳቢ ነው? የመፍትሔው አስፈላጊነትስ ምን ይመስላል ?
አቶ መላኩ ፡ በመንግሥት አስተዳደር ሂደት ውስጥ የጤና፣ የምርምር፣ የትምህርት፣ የግብርና እና የቴክኖሎጂ ዘርፎች መስፋፋትን ተከተሎ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩና የሚከማቹ በጤናና በአካባቢ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ንብረቶች መጠንና ዓይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል።
በየተቋማቱ በየዕለቱ በሚከናወኑ ሰፊ የአገልግሎትና የሥራ ሂደቶች ምክንያት ጊዜያቸው ያለፈባቸው አደገኛ ኬሚካሎች፣ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች (E-Waste)፣ የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸው መድኃኒቶች፣ የጨረራ አመንጪ ቁሳቁሶች፣ የኢንዱስትሪ ዝቃጮች እና የግብርና ኬሚካሎች መፈጠራቸው የማይቀር ተቋማዊ እውነታ ሆኗል።
እነዚህ አደገኛ ተረፈ ምርቶች ከተፈጠሩበት ጊዜ ጀምሮ በጥንቃቄ ካልተያዙ፣ ደህንነቱ በተጠበቀ ስፍራ ካልተከማቹ፣ በጥንቃቄ ካልተጓጓዙ ወይም በሳይንሳዊ መንገድ ካልተወገዱ በሰው ልጅ ጤና፣ በውሃ ሀብቶች፣ በአፈር፣ በአየር እና በብዝሃ-ሕይወት ላይ ከፍተኛ ችግር ያመጣሉ። በተጨማሪም ጥንቃቄ የጎደለው አያያዝ ተቋማቱን ለድንገተኛ የእሳት አደጋና ፍንዳታ፣ ለከፋ መመረዝ እና ለሥራ ቦታ የደህንነት ስጋቶች መዳረጋቸው አይቀርም።
ስለሆነም ይታይ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት ባለሥልጣኑ ከገንዘብ ሚኒስቴር፤ ከአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር አዲሱን የፌዴራል መንግሥት ተቋማት በጤናና በአካባቢ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ንብረቶች አያያዝ፣ አጓጓዝ፣ አጠቃቀም እና አወጋገድ ማንዋል አዘጋጅቶ ወደ ሥራ እንዲገባ አድርጓል።
********* ይቀጥላል!

0 Comments