Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

  በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ንብረቶች አያያዝ፣ አጠባበቅ እና አወጋገድ ማኑዋልዋናዋናዓላማዎች ምንድን ናቸው?

አቶ መላኩ ፡ የማንዋሉ ዋና ዓላማ በፌደራል መንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ ወይም የሚገኙ ጊዜያቸው ያለፈባቸው አደገኛ ኬሚካሎችና የኬሚካል ውጤቶች፤ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎች፤ መድኃኒቶች፤ ጨረራ አመንጭ ቁሳቁሶች፤ የኢንዱስትሪ ዝቃጮች፤ የግብርና ኬሚካሎች እና ሌሎች አደገኛ ተረፈ ምርቶች ከወጡበት እስከ መጨረሻ አወጋገዳቸው ድረስ (Cradle-to-Grave) ያለውን አጠቃላይ የሕይወት ዑደት የሰውን ጤና፣ የአካባቢ ደህንነትንና ሕጋዊ መስፈርቶችን ባከበረ መልኩ እንዲተዳደሩ የሚያስችል ወጥና የሕግ ማዕቀፎችን የተከተለ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ነው።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማኑዋሉ ዘርፈ ብዙ ዝርዝር ዓላማዎችንም ያካተተ ነው። ከእነዚህ ውስጥ የሚጠቀሱት የሚከተሉትን ይመስላሉ፡፡ በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ንብረቶች ከመነሻ መለየት፣ መመደብ፤ በየደረጃው መመዝገብ፣ ማከማቸት፣ እና ማጓጓዝ ጨምሮ እስከ መጨረሻ አወጋገዳቸው ድረስ ያለውን ሰንሰለት የተቀናጀ፣ ግልጽ እና ተጠያቂነት የተረጋገጠበት ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ፤ የመንግሥት ንብረት አወጋገድ ሥርዓት ከአካባቢ ጥበቃ መርሆዎች ጋር ማጣጣም፤ በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ንብረቶች በጥብቅ ቁጥጥርና በልዩ የአወጋገድ ሥርዓት እንዲመሩ ማድረግ፤ ከግዢ ዕቅድ ዝግጅት ጀምሮ እስከ መጨረሻ አወጋገድ ድረስ ባለው ዑደት ውስጥ የአካባቢ ተፅዕኖን መቀነስ፣ የቆሻሻ መጠንን መገደብ (Reduce)፤ መልሶ መጠቀምን (Reuse)፤ ሪሳይክል (Recycle) ማድረግን እና ዘላቂ የንብረት አጠቃቀም ባህልን በፌዴራል ተቋማት ውስጥ ማስረፅ፤ በሁሉም የፌዴራል ተቋማት ውስጥ የሚፈጠሩ፣ የሚከማቹ፣ የሚጓጓዙ እና የሚወገዱ በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ንብረቶች በተመለከተ ዲጂታላይዝ የሆነ የተሟላ መረጃ፣ የሪፖርት አቀራረብ እና የሕግ ተገዢነት ክትትል ሥርዓት መፍጠር ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ንብረቶች አያያዝ ጉድለት ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉትን የሥራ ቦታ አደጋዎች፣ የኬሚካል መፍሰስ እንዲሁም የአየር፣ የውሃ እና የአፈር ብክለትን መከላከል፤ እንዲሁም የተቋማትን ተጠያቂነት፣ ግልጽነት እና መልካም አስተዳደርን ለማጠናከር፤ በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ንብረቶች አስተዳደር ዙሪያ ግልጽ የሆነ ተግባርና ኃላፊነት መስጠት፣ የቁጥጥር ስርአት እና የአፈጻጸም መለኪያዎች እንዲኖሩ ማድረግ ነው።

 በማኑዋሉ የተጠቀሱት መሠረታዊ መርሆዎች የትኞቹ ናቸው ?

አቶ መላኩ ፡ እነዚህ ንብረቶች በአንድ በኩል ሀብት በሌላ በኩል ደግሞ መራዥ ወይም ገዳይ ናቸው። ስለሆነም ንብረቶች ጉዳት እንዳያስከትሉ ለማድረግ የሚከተሉትን ስድስት ዓለም አቀፍና አገራዊ መርሆዎች በዋና መመዘኛነት አስቀምጧል። አንደኛው የአካባቢ ብክለት አድራሽ የካሳ/የወጪ ኃላፊነት መርህ (Polluter Pays Principle)፣ ሁለተኛው ንብረቶች አያያዝ የቅድሚያ ደረጃ መርህ (Waste Hierarchy)፣ ሶስተኛው ደግሞ የቅድመ-ጥንቃቄ መርህ (Precautionary Principle)፣ አራተኛው የዙር ኢኮኖሚ ሥርዓት (Circular Economy)፣ አምስተኛው የአምራች የተራዘመ ኃላፊነት (Extended Producer Responsibility)፣ ስድስተኛውና የመጨረሻው ከመነሻ እስከ መድረሻ አስተዳደር (Cradle to Grave Management) የሚባሉ መርሆዎችን ይከተላል፡፡

 በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ንብረቶች አያያዝ፣ አጓጓዝ፣ አጠቃቀም እና አወጋገድን በሚመለከት ሀገራዊ /ብሔራዊ ሕጎች እና ዓለም አቀፋዊ ማዕቀፎች ምን ያህል ተካተዋል ?

አቶ መላኩ ፡ የተዘጋጀው ማንዋል በከፍተኛ ደረጃ ሀገራዊ /ብሔራዊ ሕጎች እና ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ መሠረት ያደረገ እንዲሁም ያካተተ ነው፡፡ ከሀገራዊ /ብሔራዊ ሕጎች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 44 ንዑስ አንቀጽ 1 ሁሉም ሰዎች ንጹሕና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት እና አንቀጽ 92 ከንዑስ አንቀጽ 1-4፣ የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 300/1995፤ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ አዋጅ ቁጥር 299/1994፤ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 513/1999፤ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016 እና መመሪያ ቁጥር 1095/2017 መነሻ ያደረገ ነው።

ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች የአደገኛ ቆሻሻዎችን ድንበር ተሻጋሪ ዝውውር የሚቆጣጠረው የባዝል (Basel) ስምምነት፤ ዘላቂ ኦርጋኒክ በካዮችን የሚያግደው የስቶክሆልም (Stockholm) ስምምነት፤ የቅድመ-ግንዛቤ ፈቃድን የሚደነግገው የሮተርዳም (Rotterdam) ስምምነት፤ እና አፍሪካን ከአደገኛ ቆሻሻ መጣያነት የሚጠብቀው የባማኮ (Bamako) ስምምነት በዋናነት የሚጠቀሱ የህግ መነሻዎቻችን ናቸው።

     ማኑዋሉ በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ንብረቶች በተመለከተ በምድብ  ከፍሏቸዋል። እነዚህ ምድቦች እና የደህንነት ስጋቶች የትኞቹ ናቸው?

አቶ መላኩ ፡ ማኑዋሉ በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ንብረቶችን በተመለከተ በስምንት ምድብ ከፋፍሎ አስቀምጧል። ምድቦችን በሚከተለው መልኩ ማስቀመጥ ይቻላል። ምድብ ሀ ተብለው የተቀመጡት ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎች ሲሆኑ በዋናነት ድንገተኛ ፍንዳታ፣ መርዛማ ጋዝ የመልቀቅ፣ የማከማቻ እቃዎችን የመብላት እና የማቃጠል አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉ ናቸው። ምድብ ለ  ኤሌክትሮኒክ ቆሻሻ (E-Waste) ነው። ይህም ከባድ ብረቶች (ሊድ፣ ሜርኩሪ፣ ካድሚየም) ወደ አፈርና ከርሰ-ምድር ውሃ ሰርገው በመግባት አፈርን፣ ውሀንና ተፈጥሮን ይበክላሉ። ምድብ ሐ ያረጁ መድኃኒቶችን ያጠቃልላል። ይህም የመድኃኒት መላመድ (AMR) ስጋት፣ የውሃ አካላት ብክለትና በሰው ላይ ፈጣን መመረዝ ያስከትላል። ምድብ መ ራዲዮአክቲቭ ቁሳቁሶችን ይይዛል። እነዚህ አደገኛ ንብረቶች በአይን የማይታይ ገዳይ ጨረር፣ የሕዋስ ማውደም፣ የጄኔቲክ መዛባትና የካንሰር አደጋን የሚያስከትሉ ናቸው።

ምድብ ሠ ስር የተቀመጡት ደግሞ የኢንዱስትሪ ዝቃጮች (Sludge) ሲሆኑ የሚያስከትሉት አደጋም በብዛት የውሃ አካላትን ብክለትና የብዝሃ-ሕይወት ውድመትን ነው፡፡ ምድብ ረ የግብርና ኬሚካሎች (POPs) የሚያጠቃልል ነው። እነዚህ ኬሚካሎች ዘላቂነት ባለው የምግብ ዋስትና እና በንቦች ህልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል። ምድብ ሰ ውስጥ የተካተቱት ያገለገሉ ዘይቶችና ቅባቶች በሚል ነው። እነዚህ አደገኛ ንብረቶች የውሃ አካላትን በዘይት ሽፋን ማፈን፣ የኦክስጅን እጥረት፣ ለካንሰር አምጪ ጭስ ልቀት ምክንያት ናቸው። የመጨረሻው ምድብ ሸ ሲሆን በዚህ ስር የተመደቡት ሊድ-አሲድ ባትሪዎች ናቸው። እነዚህ ባትሪዎች ሰልፈሪክ አሲድ የሚለቁ በመሆናቸው በልጆች አእምሮና ነርቭ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላሉ።

 ይህን ማንዋል በማስፈጸም ሂደት የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ሚና ምን እንደሆነ ቢገልጹልን ?

አቶ መላኩ ፡ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ማንዋሉን ያስፈጽማል፤ በበላይነት ይመራል፡፡ በመምራት ሂደት ውስጥ ደግሞ የህጎችን እና የማንዋሉን ተግባራዊ አፈጻጸም በየተቋማቱ በቅርብ የመከታተል፣ የመደገፍ፣ ኦዲት የማድረግ፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን የመስጠትና ሙያዊ ድጋፍ የማድረግ እንዲሁም የማንዋሉን እና ተዛማጅ ህጎችን ተግባራዊ አፈጻጸም የመከታተል ሚና አለው፡፡

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *