Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

የባለሥልጣኑን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ለማጠናከር የአመራር ውይይት እየተካሄደ ነው::

(ጥቅምት 21/2019 ዓ.ም)- የፌዴራል መንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የቀጣዮቹን አምስት ዓመታት የተቋማዊ አቅጣጫ፣ የለውጥ ቅድሚያዎችና የሚጠበቁ ውጤቶች በግልጽ ለመለየት በሚያዘጋጀው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ዙሪያ ከባለሥልጣኑ በተለያዩ የአመራር ደረጃዎች የሚገኙ አመራሮችን ያሳተፈ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።

ውይይቱ በባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ አወያይነት እየተካሄደ ሲሆን የስትራቴጂክ ዕቅዱ ከባለሥልጣኑ ሕጋዊ ሥልጣንና ተልዕኮ፣ ከተቋማዊ የለውጥ አቅጣጫ እንዲሁም ከመደመር ታላቁ ስትራቴጂ 2025–2050 ጋር በተጣጣመ መልኩ እንዲዘጋጅ ለማድረግ ነው።

በውይይቱ የባለሥልጣኑን የቀደሙ የአፈጻጸም ልምዶችና የተቋማዊ አቅም በመገምገም፣ ያሉ ጥንካሬዎችን ማስቀጠል፣ የአፈጻጸም ክፍተቶችን መለየትና ለቀጣይ የለውጥ ሥራዎች ተጨባጭ አቅጣጫ ማስቀመጥ ላይ ትኩረት ተደርጓል።

በተለይም የግዥና ንብረት ሕግና ፖሊሲ ማዕቀፍን ማጠናከር፣ የሙያ ብቃትንና ተጠያቂነትን ማሳደግ፣ የኤሌክትሮኒክ ግዥና የንብረት አስተዳደር ሥርዓቶችን ማስፋፋት፣ ዘላቂ የመንግሥት ግዥን ማሳደግ፣ የገበያና የዋጋ መረጃን ማጠናከር፣ የይግባኝና የጥቆማ አያያዝን ማሻሻል፣ የሕጋዊነት ክትትልና ቁጥጥርን ማጠናከር እንዲሁም የተቋማዊ ቅንጅትና የእውቀት ሽግግር ሥርዓትን ማሳደግ እንደ ዋና ዋና የስትራቴጂ ትኩረቶች ተነስተዋል።

የውይይቱ ዋና ዓላማ ስትራቴጂክ ዕቅዱ የአንድ የሥራ ክፍል ወይም የአመራር አካል ሰነድ ሳይሆን የባለሥልጣኑን የጋራ ራዕይ፣ ተቋማዊ ቁርጠኝነትና የወደፊት የአፈጻጸም አቅጣጫ የሚያንጸባርቅ የጋራ የሥራ መርሐ ግብር እንዲሆን ማድረግ ነው።

በዚህ ረገድ የተለያዩ የአመራር ደረጃዎች ያላቸው ልምድ፣ ዕውቀትና የሥራ እይታ በጋራ እንዲታይ፤ የሚቀረጹት ግቦችም ተጨባጭ፣ ሊለኩ የሚችሉ፣ በጊዜ የተወሰኑና በሀብት የሚደገፉ እንዲሆኑ ማስቻል እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የአመራር ውይይቱ በመደመር እሳቤ መሠረት የተለያዩ አቅሞችንና እይታዎችን በአንድ የጋራ ዓላማ ላይ በማቀናጀት፣ የባለሥልጣኑን ተቋማዊ አቅም ለማጠናከርና የሕዝብ ሀብት በብቃት፣ በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በዘላቂነት እንዲተዳደር የሚያስችል ሥርዓት ለመገንባት የሚያግዝ ነው።

ባለሥልጣኑ በውይይቱ የሚነሱ ሐሳቦችንና የማሻሻያ ምክረ ሐሳቦችን በማካተት፣ የሚቀጥሉትን አምስት ዓመታት የተቋማዊ ለውጥና የአፈጻጸም አቅጣጫ በጋራ ለመቅረጽ እየሠራ ይገኛል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *