Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

የመንግስት ግዥና ንብረት ህጋዊነት ኦዲት የመንግስትን በጀት በአግባቡ እንድንጠቀምና በጀቱ ከታለመለት ዓላማ ላይ እንዲውል በማድረግ ረገድ ያለው ሚና የጎላ ነው፡፡ አቶ አዲስ ጎዳና

(ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ሥርዓትና ቁጥጥርን በማጠናከር ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም እንዲያስገኝ የማስቻል ተልዕኮን ይዞ በከፍተኛ ትጋት እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

ባለስልጣኑ ይህን ተልዕኮን ለመወጣት የአሰራር ስርዓቶችን ከመዘርጋት ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ ተገልጋዮችንና ባለድርሻ አካላትን እያሰለጠና የጋራ ተግባቦት እንዲኖር ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ባለፉት ሁለት ቀናት  ከክልል የግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች  ለተውጣጡ ባለሙያዎች እና ለባለስልጣኑ የኦዲት ባለሙያዎች በመንግስት ግዥና ንብረት ህጋዊነት ኦዲት ላይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥ እና ንብረት አፈጻጸም እና ህጋዊነት ኦዲት እና ክትትል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አዲስ ጎዳና ሲሆኑ የመንግስት ግዥና ንብረት ህጋዊነት ኦዲት ተቋማት የመንግስትን በጀት በአግባቡ እንዲጠቀሙና በጀቱ ከታለመለት ዓላማ ላይ እንዲውል በማድረግ በኩል ያለው ሚና የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

አቶ አዲስ በስልጠናቸው የግዥ ኦዲት በተቋማት ላይ የህዝብ አመኔታን እንዲሰፍን ለማድረግ፣ የተቋማትን የግዥና ንብረት አፈጻጸም ጥራትን ለማሳደግ፣ የህግ ተገዥነትን ለማስፈን፣ ብልሹ አሰራርን ለመከላከልና ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ዋጋ ለማስገኘት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አቶ አዲስ አክለውም አንድ የኦዲት ባለሙያ ስራውን በሚፈለገው ልክና በትክክለኛው መንገድ ለማከናወን ወደ ኦዲት ስራ ከመግባቱ አስቀድሞ የግዥ ኦዲት መርሆችን ማወቅና መላበስ ይኖርበታል ሲሉ በአስንዖት የገለጹ ሲሆኑ እነዚህም ህጋዊነት፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ለገንዘብ ዋጋ መስጠት፣ ፍትሃዊነት፣ ታማኝነት፣ ተጨባጭነት፣ ነፃነት እና ሙያዊነት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ስልጠናው በተጨማሪም የኦዲት መነሻና መድረሻ፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች እና ሊወሰዱ የሚገባቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያካተተ ነበር፡፡

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *