የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በ2019 በጀት አመት የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP) ሙሉ በሙሉ ይተገብራል። አቶ አባተ ምትኩ

(ጥር 01/2018 ዓ.ም)፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአሰራር ስርዓቱን አዘምኖ ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ስራዎችን ዲጂታላይዝ የማድረግ እየሰራ ይገኛል። በዚህ ረገድ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ተጠቃሽ ሲሆን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርምን በመደገፍ በኩል ያለው ፋይዳም የጎላ ነው።
ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት ሁሉን የፌዴራል ተቋማትና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶቻቸው ግዣቸውን ሙሉ በሙሉ በመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) እንዲፈጽሙ ያስቻለ እና ወደ ክልሎችም ስርዓቱን እያስተገበረ የሚገኝ ሲሆን የግል ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ስርዓቱን መተግበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ለከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሩ እንዲሁም ለግዥና ንብረት ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል።
የስልጠናውን አስፈላጊነትና ቀጣይ ሂደትን በማስመከት ገለጻ ያደረኩት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ሲሆኑ ስርዓቱ ለትግበራ ምቹ፣ ውጢታማነትን የሚያረጋግጥ፣ ጊዜን የሚቆጥብና ታማኝነትን የሚያረጋግጥ መሆኑን አብራርተዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም የግል ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ስርዓቱን ጀምሮ ቀጣይነት እንዲኖረው በማድረግ በኩል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ድጋፉ እንደማይለየው ገለጸዋል።
በሌላ በኩል የግል ድርጅቶች ሰራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር በ2019 በጀት አመት የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP) ሙሉ በሙሉ መተግበር እንደሚገባ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አባተ ምትኩ ገልጸዋል። ዋና ስራ አስፈጻሚው እንደገለጹት ምንም እንኳ ተቋሙ ከመንግስት ተቋማት የተለዬ ባህሪ ቢኖረውም ስርዓቱ ሊያሰራ የሚችልና አንዳንድ ጉዳዮችን ተቀራርበን በመስራት የምንፈታቸው በመሆናቸው ስርዓቱን ያለማቅማማት በፍጥነት መጀመር ይኖርብናል ብለዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው በተለይም አዋጅ ቁጥር 1333/2016 እና አዋጁን ለማስፈጽም የወጡ መመሪያዎች ላይ የተካተቱ አዳዲስ ጉዳዮች እና የህግ ማሻሻያው ያስፈለገበት ምክንያት በአቶ መላኩ ተጓዴ የተብራራ ሲሆን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን በሚመለከት ደግሞ በአቶ ያፌት መኮንን ገለጻ ቀርቧል።
ከገለጻው በኋላ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች ቀርበው በባለስልጣኑ አመራር ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።








0 Comments