Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

“የተከልነው ችግኝ ብቻ ሳይሆን የነገ ተስፋችን ጭምር ነው” — ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ

(ሐምሌ 02 ቀን 2018 ዓ.ም)፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን «የነገ ተስፋን በጋራ እንትከል» በሚል መሪ ቃል የተጀመረውን ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 በሚገኘው በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (AASTU) ቅጥር ግቢ ውስጥ በተከናወነው በዚህ ንቅናቄ ከ1,000 (አንድ ሺህ) በላይ የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማና የወረዳ 09 አመራሮች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በዕለቱ የተከላ መርሃ ግብሩን በይፋ የከፈቱትና ለተሳታፊዎች መልዕክት ያስተላለፉት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በንግግራቸው ዛሬ መሬት ላይ ያረፈው ችግኝ ብቻ ሳይሆን የነገው ትውልድ ተስፋ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም የተከላ መርሃ ግብሩ ነገ አገርን የሚረከብ ትውልድ በሚገነባበት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ መከናወኑ ልዩ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ይህ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ አካባቢን ከአረንጓዴ ማልበስ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ስነ-ምህዳርን ለማስተካከል እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ፦

“ይህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement) አካልና ስትራቴጂያዊ መገለጫ ሲሆን፣ በቀጥታም ከባለሥልጣኑ ተልዕኮና የወደፊት አቅጣጫዎች ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ክቡር ዶ/ር ደረጄ እንግዳ በበኩላቸው ባለሥልጣኑ ተቋማቸውን መርጦ አረንጓዴ አሻራውን በማሳረፉ ምስጋና አቅርበው ዛሬ የተተከሉት ከ1,000 በላይ ችግኞች በልዩ ሁኔታ እንክብካቤ ተደርጎላቸው እንዲጸድቁና ምርታማ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እና የወረዳ 09 አመራሮችም፣ እንዲህ አይነት ማህበረሰባዊና አካባቢያዊ ፋይዳ ያላቸውን ብሔራዊ ጥሪዎች ተቋማት በአካባቢያቸው መጥተው ሲያከናውኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ምንጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዕለቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የባለሥልጣኑ አመራሮችና ሠራተኞች ያሳዩበት ከፍተኛ ተነሳሽነትና የወንድማማችነት ስሜት በታየበት መልኩ በስኬት ተጠናቋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *