የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዋናነት ባለስልጣኑ በትኩረት እያከናወናቸው የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን እንደ ሀገር ባለፉት ዓመታት ጀምሮ የተጀመረዉን የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ሪፎርም ሥራዎች በዝግጅት፣ በተግባር እና በማጽናት ምዕራፍ ከፋፍሎ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየፈፀመ ይገኛል፡፡ በሪፎርሙ ዝግጅት ምዕራፍ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት ለዜጎች ለማድረስ ተቋማዊ ተልዕኮዎችን ተወጥተናል ማለት ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህልም በሪፎርሙ 21 የሚጠጉ የአሠራር ሥርዓቶች በአዲስ መልክ ተዘጋጅተዉ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል፡፡
በሪፎርሙ የተግባር ምዕራፍ በዝግጅት ምዕራፍ የተዘረጉ የአሠራር ሥርዓቶችን ተጠቅሞ አገልግሎት መስጠትና አሠራሮችን በሙሉ ወደ ተግባር በመለወጥ የአገልግሎት አቅርቦት ጥራትንና ቅልጥፍናን ማሻሻል ሲሆን በሁለቱም ምዕራፎች ጠንካራ ተግባራት ተከናዉነዋል፡፡
በዋናነት በሁለቱ የሪፎርም ምዕራፎች የተከናወኑ ዓበይት ሥራዎች ስንመለከት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አደረጃጀትና አስተዳደር ሥርዓትን ለማሳለጥ የሚስችል ተቋማዊ አደረጃጀት በአዲስ መልክ ተሠርቷል፤ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ሠራተኞች የብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ሥርዓት መገንባትና የማስፈጸም አቅምን ማሳደግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቷል፤ ብዝኃነትንና አካታችነትን ያረጋገጠ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አስተዳደር ግንባታን የሚያፋጥንና ዘመናዊ የሠራተኞች አስተዳደር ስርዓት መገንባት የሚያስችል ተግባር ተከናዉኗል፤ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ተደራሽ የአገልግሎት አቅርቦት ሥርዓት ተዘርግቶ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፤ ዲጂታል የአገልግሎት አሰጣጥ እና የተደራጀ ወቅታዊ መረጃ ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም የተቋሙን ተገባራት የሚረዳ (ገቢር ነበብ) የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አመራር እና ተቋም ግንባታን ማፋጠን የሚያስችሉ የአሠራር ሥርዓቶች ተተግብረዋል፡፡
እነዚህን ጠቅለል አድርገን አነሳን እንጂ በባለስልጣኑ በእያንዳንዱ ምሶሶ ስር በርካታ ተግባራት ተከናዉነዋል፡፡ በተለይም የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ህጎችን ከአዋጅ ቁጥር 1333/2016 አንፃር በመፈተሽ ከዓለም አቀፍ ስታንደርዶች ጋር ለማጣጣም በሚያስችል መልኩ ማዘጋጀትና ከአዋጁ ጋር የተናበበ የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017፣ የልማት ድርጅቶች የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1070/2017፣ የመድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎች የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1066/2017 የመንግስት የንብረት አስተዳደር መመሪያ 1095/2017፣ የግንባታ ግዥ፣ የማዕቀፍ ግዥ፣ የምክር አገልግሎት ግዥ፣ ሌሎች አገልግሎቶች ግዥ እና የንብረት ሽያጭ የመደበኛ ጨረታ ሠነዶች (SBD) ተዘጋጅተዉ በሲስተም የማቀናጀት ሥራ ተሠርቷል፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአካል ጉዳተኞች የግዥና የንብረት የህግ ማዕቀፎችን (አዋጅ ቁጥር 1333/2016) በድምጽና በብሬን አዘጋጅቶ ተደራሽ የማድረግ ሥራም በሪፎርሙ የተከናወነ ተግባር ነዉ፡፡ ቀደም ሲል እንደተነሳው በሪፎርሙ ዝግጅት ምዕራፍ የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶች የተተገበሩ ሲሆን የተቋማዊ ለውጥ ሥራ አመራር ሥርዓት አተገባበር ማንዋል፤ የዕውቀት አስተዳደር (Knowledge Management) ማዕቀፍ መዘርጋት፤ ሠራተኞች የራሳቸውን ክፍተት በመፈተሽ አቅማቸውን ለማሻሻል የሚያገለግል የግለሰብ አቅም ማበልጸጊያ ዕቅድ (Personal Development Plan)፤ የውስጥ አሠራርና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ የአሠራር ስርዓቶች ስርዓተ ፆታና ማህበራዊ ጉዳይ ማካተቻና መከታተያ ማኑዋል ተዘጋጅቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የተግባቦት፣ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽ ሥራዎች የሚመራበት ስትራቴጂ፤ የሠራተኞችን የአመራር አቅም ግንባታ ስትራቴጂ፤ በባለስልጣኑ የሚከናወኑ የግዥና ንብረት የኦዲት ሥራዎችን ክትትልና ቁጥጥር ማሳለጥ የሚያስችል የግዥና ንብረት ክዋኔ ኦዲት ማኑዋል፤ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የውስጥ አጠቃቀም መመሪያ፤ የሲስተም ደህንነትን የሚያስጠብቅ ፖሊሲና የአሠራር ማዕቀፍ ተግባራዊነት፤ የባለስጣኑን አመራርና ሠራተኞች በብዝኃነትንና በአካታችነት ላይ ያተኮረ የአስተሳሰብ ግንባታ ሥርዓት፤ለሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር፤ ፈጣን መረጃ ሰጪዎችን (Quick Quins) (የደረት ባጅ፣ የጠረጴዛ፣ በር ላይ የሚለጠፍ መረጃ ሰጪ፣ አስተያየት መስጫ መዝገብና ሳጥን) በማዘጋጀት የተገልጋዩን አስተያየትና ጥቆማ በመቀበል ግልጽ፣ ፍትሐዊ እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል፡፡
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እያከናወናቸው ከሚገኙ ዓበይት ተግባራት አንዱ አገልግሎት አሰጣጥን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ማድረግ ነው። በዚህም በሪፎርም ሥራችን ዲጂታላይዜሽን በትኩረት እየተተገበረ ይገኛል። ዲጂታላይዜሽንን ከመተግበር አንጻር በሪፎርም ሥራው የሚከተሉት ዓበይት ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
ባለስልጣኑ የመንግስት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት (e-GP System) በየወቅቱ በመፈተሽና በማሻሻል ውጤታማነቱን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን የተሳካ ማድረግ የሚያስችል የውል አስተዳደር ሞጁል እና የንብረት ሽያጭ ማከናወን የሚያስችል ስርዓትም ሲስተሙ እንዲሠራ (configure) የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የግዥና የንብረት አቤቱታ ማጣራት እና ጥፋተኛነት ሪፖርት ሥራን በመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት (e-GP system) ለማከናወን የሚስችል የሲስተም ማሻሻያ ሥራ ማከናወን ተችሏል፡፡ የመንግስት ግዥና ንብረትን በተመለከተ ለሚቀርቡ ሙያዊ ጥያቄዎች በኤሌክትሮኒክ ምላሽ መስጠት የሚስችል አሠራር መዘርጋት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ባለስልጣኑ የተሽከርካሪ ነዳጅና ቅባት ለማስተዳደር የሚያገለግል የተሽከርካሪ ስምሪትና አስተዳደር ሥርዓትን (e-fleet management system) ተግባራዊ ማደረግ ችሏል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የባለስልጣኑን ድረ-ገጽ (www.ppa.gov.et) በአዲስ መልክ ማሻሻልና በመረጃ እንዲበለጽግ ማድረግ ተችሏል፣ በየነ መረብን (e-learning) በመጠቀም የማስተማር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት በውስጥ አቅም በማልማት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ባለስልጣኑ ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን (e-GP system) ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች የአሠራር ስርዓቶች ጋር ማስተሳሰር የቻለ ሲሆን በተለይም ከብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት (National ID)፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር (IFMIS)፣ ከባንክ፣ ከኢንሹራንስ አገልግሎት እና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ትስስር (Integration) የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፡፡
0 Comments