የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዘላቂ የመንግስት ግዥ አተገባበርን በብቃት ለመወጣት ምን እያከናወነ ነው?

እንደሚታወቀው የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአሰራር ስርዓቱን በማዘመን በአፍሪካ አርዓያ ከሆኑ የመንግስት ግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ ተቋም የመሆን ራዕይን ቀርጾ በትጋት የሚሰራ ተቋም ነው፡፡ በዚህም ሁሉንም የአገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታል ማድረግ ችሏል፡፡ በተለይም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት ሀገራችን የያዘችውን ዲጂታል ኢኮኖሚ በመደገፍ በኩል ያለው ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለስልጣኑ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ የሪፎርም የትግበራ ምዕራፍን በብቃት እየተወጣ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ በዚህ የሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ ብዙ የአሰራር ስርዓቶች የተቀረጹ ሲሆን በትግበራ ምዕራፉ ደግሞ የአሰራር ስርዓቶችን ስራ ላይ አውሏል፡፡
ስለሆነም በዚህ የዝግጅትና የትግበራ ምዕራፍ ከተከናወኑ ተግባራ አንዱ ቀጣይነት ያለው የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement manual) ማዘጋጀት ሲሆን ማኑዋሉ ተዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የማድረግ ና ስልጠና የመስጠት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገር ዘላቂ የግዥ አሠራሮች የኢንዱስትሪ ልማት የሚያረጋግጡ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን የሚያበረታቱ፣ በአካባቢ ላይ ጉዳት የማያደርሱ፣ ድህነትን ቅነሳ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ፣ የሀገሪቱን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ወይም ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲደግፉ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ዘላቂነት ያለው የመንግስት ግዥን (Sustainable Public Procurement) በሚመለከት በፌዴራል ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንደ ግዥው ባህርይ ከአካባቢ ብክለት የፀዳ፣ መልሶ መጠቀምን፣ የህይወት ዘመን ወጪ ትንተናን እና የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ከግምት ያስገባ ዘላቂነት ያለው የግዥ አፈፃፀም አሰራርን በፍላጎት መግለጫ፣ በመገምገሚያ መስፈርት፣ በውል ቃላትና ሐረጎች ዝግጅት ወቅት፣ እንዲሁም በውል አፈፃፀም ቁጥጥር ወቅት ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ያብራራል፡፡
በተመሳሳይ ይህን አዋጅ ለማስፈጸም በወጣው የፌዴራል መንግስት የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017 ክፍል ሰባት ላይ ዘላቂነት ያለው የግዥ ስርዓትን ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በተለይም ግዥው የህይወት ዘመን ወጪ ትንተና የሚሰራለት፣ የአካባቢ ጥበቃን ታሳቢ ያደረገ እና የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት ያብራራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለስልጣኑ አዋጁንና መመሪያውን ሳይሸራረፍ መፈጸም ይቻል ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ከመስጠት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡

0 Comments