የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት አካሄደ።

ጥር 07/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ቅልጥፍና ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት እና ከተገልጋዩ ማህበረሰብ ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይትና ምክክር እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ዛሬ ከመንግስት ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከግዥና ንብረት ዳይሬክተሮችና ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት የመንግስት ትልቁ በጀት ለግዥ አገለግሎት የሚውል በመሆኑ ይህን በጀት በስርዓት መምራትና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ትልቅ ሀግራዊ ሚናን እየተወጣ የሚገኝና ውጤታማነቱን ለማስቀጠል ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብልከዋል።
በሌላ በኩል ለውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ቅልጥፍና ለመጨመር አገልግሎቶችን በሙሉ ዲጂታላይዝ እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመንና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማስቻል የህግ ማዕቀፎችን መከለስና ተግባራዊ ማድረግ መቻሉንም አመላክተዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ በገለጻቸው የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ሁሉንም የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጨምሮ በሁሉም የፌዴራል የመንግስት ተቋማት ከመተግበር አልፎ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መተግበር መቻሉን ያብራሩ ሲሆን ይህም ስርዓቱ በውጤታማነት እየቀጠለ እንዳለ የሚያመላክት መሆኑን አብራርተዋል። አክለውም ሁሉም ክልሎች ስርዓቱን እንዲተገብሩት ለማስቻል እየተሰራ እንዳለና አብዛኞቹ ክልሎች የግዥና ንብረት ህጎቻቸውን ከፌዴራሉ የግዥና ንብረት ህግ ጋር የማጣጣም ስራ እየሰሩ እንደሆነ ተብራርቷል።
ባለስልጣኑ ከመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP System) በተጨማሪ የተሽከርካሪ ስምሪትና ነዳጅ ቁጥጥር (e- Fleet Management System)፣ ዲጂታል ደብዳቤ መላላኪያ (Letter Management System)፣ ዲጂታል አስተያየትና ጥቆማ መስጫ (Digital suggestion box) እና የመሳሰሉት ስራዎች ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ በማድረግ አገልግሎት ላይ እንደዋሉ ተገልጿል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው ከአነሷቸው ጉዳዮች አንዱ ተቋማዊ የሪፎርም ስራ ሲሆን የሪፎርም ስራዎች የተቋሙን ራዕይ እና ተልዕኮ ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውና የሪፎርም ስራዎችም በውጤታማነት እየተከናወኑ እንዳሉ አብራርተዋል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትንና ሌሎች የአሰራር ስርዓቶችን በውጤታማነት ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በዋና ዳይሬክተሯ እና ሌሎች የባለስልጣኑ የስራ ሀላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።







0 Comments