Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ።

(መጋቢት 22/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ባለስልጣኑ የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍናን ለማሳደግና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያገኝ ለማስቻል እየተገበራቸው ከሚገኙ የዲጂታል ስራዎች አንዱ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP system) ስርዓት ነው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን ስርዓት በሁሉም የፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲተገበር ያስቻለ ሲሆን በመንግስት የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችም ስርዓቱን እንዲተገብሩት ለማስቻል የህግ ማዕቀፎችና የአሰራር ስርዓቶች ሲሰሩ ቆይተው ዛሬ ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆሊዲንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ክቡር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እና የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ናቸው።

በፊርማ ስነ- ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ክቡር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ለማፋጠን፣ ግልጽ፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ የግዥ ስርዓት ለማስፈን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP system) ስርዓት ከፍተኛ አስተዋፆ ያለው በመሆኑ በትኩረት እንሰራበታለን ብለዋል።

በሌላ በኩል የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ባለስልጣኑ የግዥ ሂድቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

አክለውም የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ ተደራሽነትን በማስፋት፣ አሳታፊነትን በመጨመር፣ ወጪን በመቀነስ እና ግልጸኝነትን በማስፈን ረገድ ያለው ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ አመላክተዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *