Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣንና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር የመግባቢያ የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ።

(ጥር 14/2018 ዓ.ም)፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍናን ለማሳደግና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያገኝ ለማስቻል እየተገበራቸው ከሚገኙ የዲጂታል ስራዎች አንዱ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP system) ስርዓት ነው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን ስርዓት በሁሉም የፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲተገበር ያስቻለ ሲሆን ቀድመው የተገበሩትን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች እንዲተገበር ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ባለስልጣኑ ተደራሽነትን ለማስፋትና በሁሉም ክልሎች እንዲተገበር ለማድረግ በሰራው ስራ የድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር ጋር የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP system) መተግበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት የድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ እና የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ናቸው። በፌርማው ስነ- ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ እንደገለጹት የዲጂታል ኢትዮጲያን ጉዞ ለማፋጠን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP system) ስርዓት ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው አመላክተዋል። ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ በንግግራቸው የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ብልሹ አሰራርን በመቀነስ፣ ወጪንና ጊዜን በመቆጠብ ለአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በትኩረት የሚሰራበት ይሆናል ብለዋል።

በሌላ በኩል የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ባለስልጣኑ የግዥ ሂድቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት አክለውም የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ ተደራሽነትን በማስፋት፣ አሳታፊነትን በመጨመር፣ ወጪን በመቀነስ እና ግልጸኝነትን በማስፈን ረገድ ያለው ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች እንዲተገብሩት የማማከር፣ የማሰልጠንና የግዥ ህጎቻቸውን ከፌዴራሉ የግዥ ህግ ጋር የተቀራረበ እንዲሆን ለማስቻል ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

በእለቱ ከመግባቢያ ሰነዱ መፈረም በተጨማሪ የባለስልጣኑ አመራርና ሰራተኞች በድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *