Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

የመንግስት ኤሌክትሮኒክስ የግዥ ስርዓት ብልሹ አሠራርን የሚቀንስ እና ቀልጣፋ የግዥ ሂደትን ለመተግበር የሚያስችል ነው፡፡ አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)

(የካቲት 25 ቀን 2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥ ስርዓቱን በማዘመንና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚገባውን ዋጋ እንዲያገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን ሁሉንም የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በሁሉም የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ከመተግበር ባለፈ ከተማ መስተዳደሮችና ክልሎችም እንዲተገብሩት እያደረገ ይገኛል፡፡

ባለስልጣኑ አስቀድመው የጀመሩትን አዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር፣ ከሶማሊ ክልል፣ ከሀረሪ ክልል፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ከሌሎችም ክልሎች ጋር ስርዓቱ መተግበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መግባባት የተደረሰ ሲሆን ዛሬ ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በዉይይት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) እንደገለጹት የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት የግዥ ስርዓትን (e-GP System) መተግበር ዘመናዊ አሠራርን እንድንከተል ከማስቻሉም በላይ፣ ብልሹ አሰራርን የሚቀንስ እና ቀልጣፋ የግዥ ሂደትን ለመተግበር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ርዕስ መስተዳደሩ አክለዉም የመንግስት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓርትን ለመተግበር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንና በክልሉ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች እንዲተገበር ለማስቻል ድጋፍ የሚሰጥና በቅርበት ክትትል የሚደረግ መሆኑን ገልፃዋል፡፡

በሌላ በኩል የመንግስት ኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓት ምንነት፤ አላማዎችና የአተገባበር ሂደትን በሚመለከት የውይይት ሰነድ ያቀረቡት የኤፌድሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ በበኩላቸዉ ግዥን በኤሌክትሮኒክ ዘዴ መፈጸም ዉድድርንና እኩል እድልን የሚፈጥር፣ ገንዘብ የሚያስገኘዉን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስገኝ፣ የመንግስት የግዥ ህግ እንዲከበር የሚያስችሉ ዓላማዎችን ያነገበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ክብርት ወ/ሮ መሰረት አክለዉም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ የግዥ ዘዴ የግዥ ስራን በማቀላጠፍ፣ የሰነድ ማጭበርበርን በማስቀረት እና በግዥ ሂደት የተጠያቂነት ስርዓትን በማስፈን በኩል የላቀ ፋይዳ ያለዉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን በበኩላቸዉ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓትን ለመተግበር የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ የቆዩ መሆኑን ገልጸዉ በቀጣይ በክልሉ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተዉ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *