የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን ለመተግበር አናቅማማም። ወ/ሮ ልሳነወርቅ ካሣዬ

(ታህሳስ 14/2018 ዓ.ም)፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ልሳነወርቅ ካሣዬ የተመራ የከፍተኛ አምራሮች ልዑክ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለስልጣንን ጎብኝቷል። በጉብኝቱ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) በሚተገበርበት ሁኔታ ላይ ከመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።
በእለቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይ እያደረገና የሪፎርም ስራዎችንም እያከናውቀነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በተለይም ባለስልጣኑ የግዥ ሂድቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘውም የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ ተደራሽነትን በማስፋት፣ አሳታፊነትን በመጨመር፣ ወጪን በመቀነስ እና ግልጸኝነትን በማስፈን ረገድ ያለው ሚና ከፍ ያለ መሆኑን አመላክተዋል።
በተጨማሪም ባለስልጣኑ የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመን ብሎም ጥራትና ቅልጥፍናን የተቋሙ ባህል እንዲሆን ለማስቻል እየተተገበሩ የሚገኙ የአሰራር ስርዓቶች ለልዑኩ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያና አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ተጓዴ ሲሆኑ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት አዋጅ ከማሻሻል ጀምሮ የተለያዩ መመሪያዎችና የአሰራር ስርዓቶችን ስራ ላይ እንዳዋለ አመላክተዋል።
በሌላ በኩል የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ አተገባበርን፣ ዓላማ፣ ተጠቃሚ እና አጠቃላይ ይዘትና ሂደትን በሚመለከት በኢጂፒ ፕሮጀክት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ም/ማናጀር አቶ ያፌት መኮንን ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በመጨረሻም ስርዓቱን በውጤታማነት ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠባቸው ሲሆን ክልሉ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት ለመተግበር በሚያደረገው ጥረት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ድጋፉን እንደሚያጠናክር የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ገልጸዋል።










0 Comments