Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

ዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement) ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ነው ሲባል ምን ማለት ነው?

ዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement) ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚታይ አይደለም፡፡ ማለትም ግዥውን ለመፈጸም ዝቅተኛ ዋጋን እንደ መስፈረት መውሰድ በቂ አይደለም፤ የእቃውን ጥራትም እንደ ግዥ መስፈርት ወስዶ ግዥውን መፈጸም በቂ አይደለም፡፡ ይልቁንም ግዥውን ለመፈጸም ከላይ ከገለጸናቸው መስፈርቶች በተጨማሪ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሚታ፣ በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ የማያሳድር መሆኑ፣ ማህበራዊ አገልግሎት ላይ ያለው አስተዋጽዖ፣ አረንጓዴ ልማትን መድገፍ የሚያስችል መሆኑና ሌሎች መሰል መስፈርቶች ከግምት ውስጥ የሚገቡ ናቸው፡፡ በዝርዝር ለመመልከት ያህል፦

የኢኮኖሚ ዘላቂነት (Economic sustainability) የኢኮኖሚ ዘላቂነት በምርቶች እና በአገልግሎቶች የህይወት ዑደት ውስጥ ለተከፈለው ገንዘብ ተመጣጣኝ ዋጋ (Value for Money) ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል። ይህም የወጪ ውጤታማነትን (Cost efficiency)፣ የጥራት ማሻሻያን (Quality improvement)፣ ዘላቂነትን (Durability)፣ የጥገና ወጪ መቀነስን  (Reduction of maintenance costs) እና የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ቁጠባን (Long-term financial savings) መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ሂደት ውስጥ የግዥ ባለሙያዎች የመግዣ ዋጋ ላይ ብቻ  አያተኩሩም ይልቁንም ከመግዣ ዋጋው በተጨማሪ የሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን፣ የጥገና ወጪዎችን እና የማስወገጃ ወጪዎችንም ግንዛቤው ውስጥ ያስገባሉ።

የአካባቢ ዘላቂነት (Environmental sustainability) የአካባቢ ዘላቂነት የግዥ ሂደቶች ግዥው በአካባቢ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ ላይ ያተኩራል። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርነው የሚገዙ ግዥዎች በአካባቢ ላይ ብክለትን የማያስከትሉ መሆናቸው መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይህን ስንል የሚገዙ ምርቶች ብክለትን የሚቀንሱ፣ ኃይልን የሚቆጥቡ፣ እንደገና ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ቁሳቁሶችን የሚጠቀሙ፣ የግሪን ሀውስ ጋዞችን የሚቀንሱ እና ታዳሽ ኃይልን የሚያበረታቱ መሆናቸው ግንዛቤ ውስጥ መግባት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም የአካባቢ ተስማሚ ግዥ (Environmental Sustainability Procurement) የአየር ንብረት ለውጥን ለመቀነስ እና የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠበቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል።

ማህበራዊ ዘላቂነት (Social Sustainability):- ማህበራዊ ዘላቂነት የማህበራዊ ደህንነትን ለማሻሻል እና ሥነ-ምግባራዊ የንግድ አሠራሮች ማረጋገጥ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ፍትሃዊ የሥራ ልምዶች፣ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ፣ የሥራ ቦታ ደህንነት፣ የፆታ እኩልነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ለተጋላጭ ቡድኖች ድጋፍ መስጠትን የሚያበረታታ ነው፡፡

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *