Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ::

(ሰኔ 26/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች፣ የንብረት ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም የተሸከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ሥራ አስፈጻሚዎች እን ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በኢ-ፍሊት (e-Fleet Management System) ትግበራ እና በመንግስት ንብረት አወጋገድ አፈጻጸም ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

 

በመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የውይይት መድረኩ በሀገራችን የመንግስት ንብረትና የተሸከርካሪ አስተዳደር ሥርዓትን የበለጠ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂ እና ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው የለውጥ ጉዞ ውስጥ አንዱ አስፈላጊ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል። ዋና ዳይሪክተሯ አያይዘውም የንብረት አያያዝና አወጋገድ ስርዓቱም ከባቢን በማይበክል እና መልሶ መጠቀምን በሚያበረታታ መልኩ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

የንብረት አያያዝንና አወጋገድን አፈጻጸምን አስመልክቶ ገላጻ ያቀረቡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያ እና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላክ ተጓዴ በበኩላቸው የመንግስት ተቋማት ያሉባቸውን የአፈጻጸም ክፍተቶች መለየት ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ አገልግሎት የማይሰጡና የተከማቹ ንብረቶችን በተገቢው ሒደትና ፍጥነት ማስወገድ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲሁም የንብረት አያያዝንና አወጋገድን ለማሻሻል እየተወሰዱ ስላሉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን አብራርተዋል።

አቶ መላኩ በማብራሪያቸው አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች በወቅቱ ካልተወገዱ የማከማቻ ወጪ እንደሚያስከትሉ፣ የንብረት መዝገቦችን እንደሚያዛቡ፣ የሥራ ቦታዎችን እንደሚያጨናንቁ እና የሙስና ተጋላጭነትን የሚጨምሩ በመሆናቸው በሕግና በመመሪያዎች መሠረት መፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

በሌላ በኩል የኢ-ፍሊት (e-Fleet) ሥርዓት አጠቃቀምንና ተያያዥ አፈጻጸሞችን በተመለከተ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP Project) ማናጀር አቶ ያፌት መኮንን ዝርዝር ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ሥርዓቱ በመንግስት ተሸከርካሪዎች አስተዳደር ውስጥ ግልጽነትን ለማሳደግ፣ ወጪን ለመቆጣጠር እና ውሳኔዎችን በመረጃ ላይ ተመስርተው እንዲወሰኑ ለማድረግ የተዘረጋ መሆኑ ተገልጿል።

ከቀረቡት ገለጻዎች በኋላ ከተሳታፊ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ለቀረቡት ጥያቂዎችና አስተያየቶች የማጠቃለያ ማብራሪያ የሰጡት የመንግስት ሀብት የህዝብ ሀብት በመሆኑ በአግባቡ መጠቀምና መጠበቅ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን በቀጣይም ተቋማቱ የኢ-ፍሊት ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ፣ መረጃዎችን ወቅታዊ እንዲያደርጉ፣ የንብረት አወጋገድ ሂደቶችን በወቅቱ እንዲያስፈጽሙ እና የአመራር ክትትልን እንዲያጠናክሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በዚሁም ተጠያቂና ዘመናዊ የንብረት አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ በመደረስ ውይይቱ በስኬት ተጠናቋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *