Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

«ችግኝ መትከል ለአረንጓዴ ኢኮኖሚና ለዘላቂ ግዥ እውን መሆን ወሳኝ ነው» — ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ

(ሀምሌ 28/2018 ዓ.ም) አዲስ አበባ — የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብሩ አካል አድርጎ 8 ሺህ ችግኞችን የመትከል የተቀናጀ ንቅናቄ እያካሄደ ይገኛል።
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ከ1,000 በላይ ችግኞችን የተከለ ሲሆን ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከተጠሪ ተቋማት ጋር በተካሄደው የጋራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም በግንባር ቀደምትነት በመሳተፍ አሻራውን አኖሯል።

የዚሁ ንቅናቄ ቀጣይ አካል የሆነውና 7,000 ችግኞች የተተከሉበት ታላቅ መርሃ ግብር ሐምሌ 28 ቀን 2018 ዓ.ም በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ በደመቀ ሁኔታ ተካሂዷል። ይህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተስፋን እንትከል በሚል መርህ «በአንድ ጀንበር 800 ሚሊዮን ችግኝ» ለመትከል የያዘችውን ታላቅ ዘመቻ የሚያግዝ እና የተቋሙን አካባቢያዊ ኃላፊነት የሚያሳይ ነው።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት ችግኞችን መትከልና መንከባከብ የሀገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ፣ የከፋውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመታደግ እና የጸና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታን ለማረጋገጥ ወሳኝ ድርሻ ብለዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ይህ የችግኝ ተከላ ንቅናቄ ባለስልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራበት «ዘላቂነት ያለው ግዥ» (Sustainable Procurement) እሴቶች ጋር በቀጥታ የተያያዘ መሆኑን ጠቁመው የአካባቢ ጥበቃን ከግዥ ሥርዓቱ ጋር በማቀናጀት ዘላቂነት ያለው ሀገራዊ ልማትን እውን ለማድረግ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ዋና ዳይሬክተሯ ባለስልጣኑ በ2017 በጀት ዓመት በዚህ ከተማ ከ25000 ችግኞችን እንደተከለ አስታውሰው ማህበረሰቡ እንዲንከባከባቸው አሳስበዋል።

ተቋሙ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የማህበረሰብ አቀፍ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን አጣጥሞ በማስኬድ ረገድ አርአያነቱን እያሳዬ ይገኛል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *