ባለስልጣኑ የፌደራልመንግስትግዥናንብረትየህጋዊነት ኦዲት ማንዋል ተግባር ላይ እንዲውል ወሰነ።
የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1333/2016 የተሰጠውን ሀላፊነት ለመወጣት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። በተለይም አዳዲስ መመሪያዎች በገንዘብ ሚኒስቴር ወጥተው እንዲተገበሩ በማድረግ ደረጃ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎች ማኑዋሎችንና የአሰራር ስርዓቶችን በመቅረጽ ወደ ስራ አስገብቷል።
ባለስልጣኑ በቅርብ አጽድቆ ወደ ተግባር እንዲገቡ ከአደረጋቸው ማኑዋሎች አንዱ የፌደራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የህጋዊነት ኦዲት ማንዋል ይገኝበታል።
ሰነዱ ምን ጉዳዮችን ይዟል?
ይህ ሰነድ በአምስት ክፍሎች እና በ82 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን የግዥና ንብረት አስተዳደር ኦዲት አጠቃላይ መግለጫ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኦዲት ዓላማዎች፣ ግቦች፣ ተግባራት፣ መርሆዎች እና እሳቤዎች፣ የተሳታፊ አካላት ስልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነት፣ የግዥና ንብረት ኦዲት ክንውን ዑደት እና የኦዲት ማከናወኛ ሰነዶች በአባሪነት አካትቷል።
በመጀመሪያው ክፍል የመንግስት ግዥና ንብረት ኦዲት ፋይዳ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኦዲት ባለድርሻ አካላት እና በኦዲት ስራ ወቅት ሊደረጉ የማይገቡ ተግባራት በስፋት ተብራርተዋል።
በሁለተኛው ክፍል በተለይም የኦዲት ዓላማዎች በግልጽ የተብራሩ ሲሆን የመንግስት የግዥና ንብረት የሕግ ማዕቀፎችን ተከትሎ የተፈጸመ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ገንዘብ ሊያስገኝ የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ (Value for Money) ማስገኘቱን ማረጋገጥ፣ ሙስና፣ ብልሹ አሰራር እና የመልካም አስተዳደር ችግርን መከላከልና ማጋለጥ፣ ግልጸኝነትና ፍትሃዊነት ውድድር መኖሩን ማረጋገጥ፣ የመንግስት ንብረትን መጠበቅ፣ ተጠያቂነት መኖሩን ማረጋገጥ፣ የግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር ሥራዎች እንዲሻሻሉ እገዛ ማድረግ የሚሉ አበይት ጉዳዮችን የያዘ ነው።
በዚህ ክፍል ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ የኦዲት ግቦች፣ ኦዲቱ የሚያካትታቸው ተግባራት፣ የኦዲት መርሆዎች እና እሳቤዎች በተለይም ገለልተኛነት (Independence)፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ህግና ዓለም አቀፍ የኦዲት ስታንዳርድ መከተል (Compliance with Laws & Standards)፣ ሙያዊ ስነ-ምግባር /Professional Ethics/፣ የኦዲት የሥራ ማህደሮች (Audit Working Papers) እና ተያያዥ ጉዳዮች በስፋት ተብራርተዋል።
በሞጁሉ ሦስተኛው ክፍል ስልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነት የያዘ ሲሆን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን፣ የኦዲት ተደራጊ ባለበጀት መ/ቤቶች፣ የግዥና ንብረት ኦዲት የሥራ ክፍል የኦዲት ባለሙያዎች ስልጣን፣ ተግባርና ሀላፊነትን ይዟል።
አራተኛው የሞጁሉ ክፍል የግዥና ንብረት ኦዲት ክንውን ዑደትን የያዘ ሲሆን የኦዲት ቅድመ ዝግጅት፣ የህጋዊነት ኦዲት ክንውን፣ የኦዲት ሪፖርት ዝግጅት፣ ቁጥጥር እና ክትትል አካትቷል።
የመጨረሻው የሞጁሉ ክፍል የኦዲት ማከናወኛ ሰነዶች የያዘ ሲሆን የተተመነውን ሰዓት ሥራ ላይ ከዋለው ሰዓት ጋር ማነፃፀሪያ፣ የሙያ ሥነ-ምግባር መከታተያ ቅጽ፣ የኦዲተሮች የቡድን ብቃት ስብጥርን ያሚያሳይ ቅጽ፣ የኦዲት የሥራ ስምምነት ደብዳቤ እና ተያያዥነት ያላቸውን ሰነዶች ይዟል።
ለበለጠ መረጃ፤
ድረ ገጽ፡ https://www.ppa.gov.et/
ፌስቡክ፡ Public Procurement and Property Authority
ቴሌግራም፡ Public Procurement and Property Authority/የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

0 Comments