ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ

(ሰኔ 18/2018 ዓ/ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የንብረት ማስወገድ ሂደት እና የኢፍሊት ማናጅመንት (e-Fleet Management) አተገባበርን በሚመለከት ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በንግግራቸው የመንግስት ሀብትና ንብረትን በቁጠባ፣ በግልጽነትና በብቃት ማስተዳደር ያለውን የላቀ ጠቀሜታ ያብራሩ ሲሆን የተሽከርካሪ ስምሪትና ነዳጅ አጠቃቀም ስርዓትንም በጥብቅ ስነ- ምግባር መተግበር እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
የንብረት አያያዝና አወጋገድን በሚመለከት ገለጻ ያቀረቡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያ እና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላክ ተጓዴ በበኩላቸው የመንግስት ተቋማት ያሉባቸውን የአፈጻጸም ክፍተቶች መለየት ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ አገልግሎት የማይሰጡና የተከማቹ ንብረቶችን በተገቢው ሒደትና ፍጥነት ማስወገድ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲሁም የንብረት አያያዝንና አወጋገድን ለማሻሻል እየተወሰዱ ስላሉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የተሽከርካሪ ስምሪት እና ነዳጅ አጠቃቀም ስርዓትን (e-Fleet management Sysytem) አፈጻጸምና አሁናዊ ሁኒታን በሚመለከት የኢጂፒ (e-GP) ፕሮጀክት ጽ/ቤት ማናጀር አቶ ያፌት መኮንን ገለጻ ቀርቧል። አቶ ያፌት በገለጻቸው በፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ላይ ያለው የኢፍሊት ማናጅመንት አፈጻጸም ያለበትን ተጨባጭ ሁኔታ እንዲሁም ስርዓቱ የመንግስት ተሽከርካሪዎችን ቁጥጥር ለማዘመን፣ የነዳጅና የጥገና ወጪን ለመቀነስ ብሎም ግልጽነትን ለማስፈን እያበረከተ ስላለው አስተዋጽኦ እና ስርዓቱ ያለበትን የትግበራ ደረጃና በቀጣይ ሊሻሻሉ ስለሚገባቸው ጉዳዮች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በእለቱ የሙስና ተጋላጭነት ስጋት ጥናትም በስነ- ምግባርና ጸረ- ሙስና ኮሚሽን ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የቀረቡትን ገለጻዎች መነሻ በማድረግ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበዋል። በመጨረሻም በክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እና ባለደረቦቻቸው የጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ የእለቱ ውይይት ተጠናቋል።






0 Comments