Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

ባለስልጣኑ ከሲዳማ ክልል ለተውጣጡ አመራሮች የሪፎርም ትግበራ ልምዱን አካፈለ።

(ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥ እና ንብረት ባለስልጣን ከሲዳማ ክልል ለተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች የተቋሙን የአስተዳደርና አገልግሎት ማሻሻያ ሪፎርም አተገባበር ልምድ እና ያገኛቸውን በጎ ውጤቶች አካፈለ።

በመድረኩ ላይ የሪፎርም አፈጻጸም ሰነዱን ያቀረቡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት ተቋሙ የሪፎርሙን የትግበራ ጊዜን በውጤታማነት እየተወጣ የሚገኝ የገለጹ ሲሆን አሁን ላይ የተገኘውን ስኬት ወደ ማጽናት ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ሰፋፊ ተግባራትን እያከናወነ አብራርተዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ባለስልጣኑ በተለይም የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት፣ ተቋማዊ አደረጃጀትን በማስተካከል፣ የሰው ሀይልን በብቃት ማበልጸግ እና አሰራሮችን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ በማድረግ ረገድ ጠንካራ እና ለዋጭ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቁመዋል።

ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ የሪፎርም ትግበራው ዋና ዋና አፈጻጸሞች እና የተገኙ ውጤቶችን በተለይም የህግ ማዕቀፎች እና የአሰራር ስርዓት ማሻሻያን በገለጹበት ገለጻ አዲሱን የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016 መነሻ በማድረግ የግዥ አፈጻጸም፣ የመድኃኒትና ህክምና መሳሪያዎች፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች እና የንብረትና ተሸከርካሪ አስተዳደር መመሪያዎች ተዘጋጅተው በስራ መዋላቸውን እና የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ የጨረታ መደበኛ ሰነዶች (SBD)፣ የአቤቱታና ይግባኝ አቀራረብ ማንዋሎች እንዲሁም ዘላቂነት ያለው የግዥ ስርዓት (Sustainable Procurement) ማንዋል ተዘጋጅተው ስራ ላይ እንደዋሉ አመላክተዋል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዥ (e-GP) ስር ዓት ትግበራ፣ የተሸከርካሪ ቁጥጥር እና ንብረት ቁጥጥር (e-Fleet) እና ሌሎች ዲጂታል ስራዎችን በከፍተኛ ዲስፕሊን እየተገበረ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

ባለስልጣኑ የሪፎርም ውጤታማነቱን ለማስቀጠል የሰው ሀይል ብቃትን ማሳደግ እንዲሁም ብዝኃነት እና አካታችነት መተግበር አስፈላጊ በመሆኑ ሰራተኞችን የማብቃትና አካታችነቱን እንዲጠብቅ የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተብራርቷል።

በቀጣይም ባለስልጣኑ እስካሁን ያገኛቸውን የዲጂታላይዜሽን እና የተቋማዊ ሪፎርም ስኬቶች በማጠናከር፣ የዲጂታል አሰራሩን ወደ ሁሉም ክልሎች የማስፋፋት፣ የአገልግሎት ጥራትን የማሳደግ እና ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራርን የመገንባት ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን የሲዳማ ክልል አመራሮችም ባለስልጣኑ እየተገበረ በሚገኘው የሪፎርም ስራ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *