ባለስልጣኑ “ከምርጫ ማግስት: ጠንካራ መንግስት” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት አካሄደ።

(ሰኔ 12/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ፡ ከዜግነት ግዴታ እስከ ተቋማዊ እምርታ በሚል መሪ ሀሳብ ከሰራተኞች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ሲሆኑ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የሁሉም ሰራተኛ ሀላፊነት መሆኑን አመላክተው ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሰራተኛው የህዝብን ፍላጎት የሚያሳካ፣ የመንግስትን ንብረት የሚጠበቅ፣ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጥ፣ ሀገራዊ ትልሞችን አውቆ የሚተገብር መሆን አንዳለበት ገልጸዋል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት መንግስት ሰላምና መረጋጋት የማረጋገጥ፣ ፖለቲካዊ ውጥረቶችን በውይይት የመፍታት፣ የተቋማትን አቅም የማጎልበት፣ የህዝብን ጥያቄ የመመለስ፣ ዲጂታል ስራዎችን በትኩረት የመተግበር፣ ተቋማትንና የሰራተኞችን አቅም ማጎልበት ላይ በትኩረት የሚሰራ ሲሆን እንደ ተቋም ተገቢውን የቁጥጥር ስራ በትኩረት መስራት፣ ኢፍሊት ማናጅመንትን ወደ ተሟላ ትግበራ ማስገባት፣ ተቋማትን መደገፍ፣ ዲጂታል ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናን ማረጋገጥ፣ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ዳር ማድረስ እና ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መከላከል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሚኒሊክ ሳሙኤል በበኩላቸው ከምርጫ ማግስት መንግስትነትን የሚረከበው ፓርቲ አሸናፊነትን እንደ ድል ሳይሆን እንደ ድርብ ሀላፊነት ወስዶ ሀገር የጀመረችውን ሁለንተናዊ እድገት ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በተለይም ተቋማዊ አገልግሎትን ማጠናከር፣ የዜግነትና ተቋማዊ ሀላፊነትን ማሳደግ እንዲሁም ሀገረ መንግስትን ማጽናት ላይ በትኩረት ማስራት እንደሚያስፈልግ ያመላከቱ ሲሆን ሰራተኞች የተሰጣቸውን ሀላፊነት በአግባቡ በመወጣት ለሀገረ መንግስት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ መወጣት አለባቸው ብለዋል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰጥተው በተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ ውይይቱ ተጠናቋል።





0 Comments