ባለስልጣኑ በአስተዳደራዊ ቅጣት ረቂቅ መመሪያ ላይ ከፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

(መጋቢት 23/218)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግሥት ግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት የሚወሰዱ አስተዳደራዊ ቅጣቶች አፈፃፀም ረቂቅ መመሪያ ላይ ከፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ ከግዥና ንብረት ሀላፊዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
በውይይቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ መመሪያው የተጠያቂነት መላላትን ለማስቀረት፣ ጠንካራ የህግና የአሰራር ስርዓትን ለመፍጠር፣ ብልሹ አሰራርን እንዲወገድ ለማድረግ እንዲያስችል ተደረጎ መዘጋጀቱን ተናግረው፤ በረቂቅ መመሪያው ላይ ግልፅ ውይይትና ግንዛቤ መፍጠር በማስፈለጉ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የውይይት መነሻ ጽሁፉን ያቀረቡት በገንዘብ ሚኒስቴር የህግ መመሪያ ሀላፊ አቶ ተወዳጅ መሀመድ በበኩላቸው ይህ መመሪያ እንዲወጣ አስቀድሞ በአዋጅ 1333/2016 የተቀመጠ ሲሆን መመሪያው በየደረጃው ያሉ ከግዥና ንብረት ጋር የተገናኙ ሀላፊዎችንና ባለሙያዎችን ሀላፊነት እንዲወጡ ለማስቻል ብሎም የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አስተዳደር ስራው በሀላፊነት እንዲሰራ ለማስቻል የተዘጋጄ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ረቂቅ መመሪያው በማንኛውም የመንግስት መ/ቤት የተሾመ ወይም የተመደበ ሰው ከግዥ አፈፃፀም እና ንብረት አስተዳደር ጋር በተገናኘ ዓመታዊ የግዥ ዕቅድን፣ የግዥ አፈጻጸም ሪፖርቶችን፣ የንብረት አስተዳደር ሪፖርት በተገቢው የጥራት ደረጃና ግዜ ካላቀረበ እንዲሁም ጥቅም ላይ የማይውሉ እና አገልግሎታቸውን የጨረሱ ንብረቶችን በወቅቱ አለማስወገድ ወይም እንዲወገዱ አለማድረግ እና ሌሌችንም ዝርዝር ጥፋቶችን አካቷል፡፡
ረቂቅ መመሪያው የተዘረዘሩትን ጥፋቶችን ፈፅሞ የተገኘ የስራ ኃላፊና ተሿሚ እንደጥፋት ደረጃውና ድግግሞሹ የተለያዩ ማስጠንቀቂያና የገንዘብ መቀጫ እንደሚጣልበት ያብራራል፡፡
በውይይቱ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በክብርት ዋና ዳይሬክተሯ እና በሚመለከታቸው የባለስልጣኑ የስራ ሀላፊዎች ምላሽና መብራሪያ ተሰጥቶባቸው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡






0 Comments