ባለስልጣኑ በተቋሙ የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ላይ ውይይት አካሄደ።

(መጋቢት 20/ 2018)፣ የኢፌዴራ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከ2016-2018 መካከለኛ ዘመን እቅድ መጠናቀቁን ተከትሎ ከአስር ዓመቱ ስትራቴጂ እቅድ የተቀዳ አዲስ የመካከለኛ ዘመን (2019-2022) እቅድ አዘጋጅቷል።
ባለስልጣኑ ሰነዱን በማኔጅመንት ገምግሞ ሲያዳብር ቆይቶ ዛሬ ከባለስልጣኑ ሰራተኞች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት ያለፈው የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ ውጤታማ ነበር። ስለሆነም ከባለፈ የእቅድ አፈፃፀም በመነሳት ለበለጠ ስኬት መትጋት ይኖርብናል ብለዋል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት በንግግራቸው በተለይም ይህ እቅድ የ10 ዓመቱ ስትራቴጂ እቅድ የመጨረሻው በመሆኑ ለስትራቴጂክ እቅዱ ስኬት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ያመላከቱ ሲሆን እቅዱን በትልቅ የአዕምሮ ዝግጁነትና ስነ ምግባር መፈጸም እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት በቀጣይ ዓመታት በተለይም ዲጂታል የግዥና ንብረት ስርዓትን ማጠናከር፣ የአልግሎት አሰጣጥ ግልጸኝነትን ማስፈን፣ የባለድርሻ አካላትን ትስስር ማጠናከር፣ የመረጃ ተደራሽነትን ማሳደግ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል።
የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያ እና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ተጓዴ ሲሆኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት (2016-2018) በርካታ የአሰራር ሥርዓቶች እንደተዘረጉ፣ ዲጂታል አገልግሎትን ለማስፋት ሰፋፊ ስራዎች እንደተከናወነ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፋፊ ስራዎች መሰራታቸዉንና የተገልጋይ እርካታን የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን ብሎም ሰፋፊ የሪፎርም ስራዎች መከናዎናቸውንና በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን አመልክቷል ።
አቶ መላኩ አዲሱን የመካከለኛ ዘመን ዕቅድ (2019-2022) ዋና ዓላማ ባለስልጣኑ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓትን በማጠናከር ከአፍሪካ ቀዳሚ የመንግስት ግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ ሆኖ የመገኘት ራዕይን እውን ማድረግ ሲሆን ዲጂታላዜሽንን ማጠናከር፣ ተቋማዊ አቅምን ማጎልበት፣ ዘላቂ ግዥና ንብረት ስርዓትን ማጠናከር፣ የመረጃና አገልግሎት ጥራትን ማሳደግ፣ የፖሊሲ፣ ማማከርና የምርምር ስራን ማጠናከር፣ ስትራቴጂካዊ ትብብርን ማጠናከር፣ የይግባኝን ጥፋተኝነት ስርዓትን ማጠናከር እንዲሁም የኦዲትና ክትትል ስራን ማጠናከር የሚሉ ዝርዝር ዓላማዎች እንዳካተተ አብራርተዋል።
አቶ መላኩ በማጠቃለያ ንግግራቸው የባለስልጣኑ ስኬት የሚለካው በእቅድ ብቻ ባለመሆኑ ለእቅዱ ስኬት ሁሉም በተሰጠው ሀላፊነት ልክ በትጋትና በቅንነት ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በመጨረሻም ከሰራተኞች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን በክብርት ዋና ዳይሬክተሯ እና በሚመለከታቸው ስራ አስፈፃሚዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል። ምላሽና ማብራሪያውን ተከትሎ የቀሪ ወራት የስራ አቅጣጫ በክብርት ዋና ዳይሬክተሯ ክብርት ወ/ሮ መሰረት የቀጣይ ወራት የስራ አቅጣጫ የተሰጠ ሲሆን በተለይም ከኦዲትና ቁጥጥር፣ ከዲጂታል አገልግሎት እንዲሁም ከአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበት አቅጣጫ ተሰጥቶ ውይይቱ ተጠናቋል።









0 Comments