ባለስልጣኑየኮንትራትማኔጅመንትአቅምንለማጠናከርያለመስልጠና እየሰጠ ነው።

(ሀምሌ 10/2018 ዓ.ም)፣ የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በገጠር ትሥር ኮኔክቲቪቲ (Rural Connectivity) ፕሮግራም ማዕቀፍ ውስጥ የሚፈጸሙ የኮንትራት ፕሮጀክቶችን በተሻለ ብቃት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ለመምራት የሚያስችል ሀገራዊ የኮንትራት ማኔጅመንት ስልጠና መድረክ ከፍቷል።
የስልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት ይህ መድረክ በክልል መንገድ ዘርፍ፣ በፋይናንስ ተቋማት እና በክልል ግዥ ባለስልጣናት መካከል የጋራ ግንዛቤን ለማጠናከርና በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያለመ መሆኑን አመላክተዋል።
ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ በንግግራቸው የገጠር ትስስር (Rural Connectivity) ፕሮግራም የገጠር ማህበረሰቡን ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች ጋር በማገናኘት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ወሳኝ ሀገራዊ ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰዋል። የገጠር መንገዶችና የመጓጓዣ መሠረተ ልማቶች የገበያ ተደራሽነትን፣ የግብርና ምርትን፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎትን እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራን የሚያፋጥኑ መሠረታዊ የልማት መሣሪያዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል።
“እያንዳንዱ የሚገነባ ኪሎ ሜትር መንገድ በዜጎቻችን የኑሮ ጥራት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው” ያሉት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የፕሮጀክቶች ስኬት ግን በጀት በመመደብ ብቻ እንደማይረጋገጥ ይልቁንም ጥራት ያለው የግዥ ሂደት፣ ውጤታማ የኮንትራት አስተዳደር፣ ወቅታዊ ክትትል፣ ትክክለኛ የፋይናንስ አያያዝ እና ጠንካራ የተቋማት ቅንጅት በአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ዛሬ በአለም አቀፍ ደረጃ የመንግስት ግዥ ዓላማ ከዝቅተኛ ዋጋ አሰራር ወጥቶ ወደ “Value for Money” (ለገንዘብ ተገቢውን ዋጋ ማግኘት)፣ ዘላቂነት፣ እና የህይወት ዑደት ወጪ ትንተና (Life Cycle Cost Analysis) ላይ ትኩረት እያደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። ባለስልጣኑም ይህንን መሠረት በማድረግ የግዥ ሥርዓቱ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተወዳዳሪና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን የህግ ማዕቀፎችንና የቴክኖሎጂ አሰራሮችን በመዘርጋት የተቋማትን አቅም ለመገንባት በስፋት እየሰራ ይገኛል።
በውይይቱ በኮንትራት ማኔጅመንት ውስጥ የለውጥ ትዕዛዞችን (Variation Orders) በአግባቡ ማስተዳደር፣ የጊዜ ማራዘሚያ ጉዳዮችን በአግባቡ መመርመር እና ክፍያዎችን በግልጽነት መፈጸም የፕሮጀክቶችን ስኬት እንደሚወስኑ የተገለጸ ሲሆን ሊያጋጥሙ የሚችሉ የዋጋ መለዋወጥ፣ የአየር ጸባይና የቴክኒክ ስጋቶችን (Risks) ቀድሞ በመለየት የጥንቃቄ ስልቶችን ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።






0 Comments