Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

ባለሥልጣኑ የዲጂታላይዜሽንና የተቋማዊ ማሻሻያ ሥራዎቹን ገመገመ።

(ሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም.)፣ የፌዴራል ግዥና ንብረት ባለሥልጣን (FPPA) ተቋማዊ አሠራሩን ለማዘመንና የዲጂታላይዜሽን ክንውኑን ለማሳካት ያለሙ ሦስት ወሳኝ የአሠራር ማዕቀፎችና ሥርዓቶች ላይ ከአመራር አባላት እና ከቡድን መሪዎች ጋር ሰፊ የውይይትና የግምገማ መድረኮችን አካሂዷል።

የመጀመሪያው ውይይት የኤሌክትሮኒክ የፍሊት ማኔጅመንት (e- Fleet Management) ሥርዓት አፈጻጸም ላይ ያተኮረ ነበር። በመድረኩም ባለሥልጣኑ በፌዴራል መንግሥት ተቋማት ውስጥ ተግባራዊ የተደረገውን የኤሌክትሮኒክ የፍሊት ማኔጅመንት ሥርዓት (e- Fleet Management) የአፈጻጸም ደረጃ ገምግሟል።

ለውይይት የቀረበው ሌላው ጉዳይ የኢ-ጂፒ (e-GP) መረጃና ሰነድ አስተዳደር ረቂቅ ማንዋል ነው። በማኑዋሉ ባለሥልጣኑ በኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ (e-GP) ሥርዓት ውስጥ የሚፈጠሩ መረጃዎችንና ሰነዶችን በትክክል ለመያዝና ለማስተዳደር የሚያስችል አዲስ የአሠራር ረቂቅ ማንዋል መሆኑ ተጠቁሟል።

ሁለቱንም የውይይት መነሻ ጽሁፎች ያቀረቡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ያፌት መኮነን ሲሆኑ የኢ-ጂፒ (e-GP) መረጃና ሰነድ አስተዳደር ረቂቅ ማንዋሉ በኢ-ጂፒ ሥርዓት ውስጥ የሚመነጩ መረጃዎችን ሙሉ የሕይወት ዑደት (ከአፈጣጠር እስከ አወጋገድ) በሕጋዊና በቴክኖሎጂ ማዕቀፍ ለመምራት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል። ሥርዓቱ የውሂብ ባለቤትነትና ጠባቂነትን፣ የዲጂታል ፊርማ አስተዳደርን፣ የሳይበር ደህንነት ጥበቃን እና የሰነዶች ማቆያና ማስወገድ ሥርዓትን ለይቶ በማስቀመጥ የትግበራ ውጤታማነትን እንደሚያረጋግጥ ተገልጿል።

ባለስልጣኑ ውይይት ያደረገበት ሌላው ጉዳይ የተቋማዊ ሰነድ አስተዳደር ሥርዓት (Record Management System) ማሻሻያን በሚመለከት ነው። ይህ ሰነድ ባለስልጣኑ እየተገበረው ያለው የተቋማዊ ማሻሻያ እና የዲጂታላይዜሽን የትግበራ አካል ነው።

የዚህን መነሻ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት አቶ ጸጋዬ አበበ ሲሆኑ ጠንካራ የሰነድ አስተዳደር ሥርዓት መኖሩ ለተቋማዊ ግልጽነትና ለሥራ ቅልጥፍና መሠረት መሆኑን ገልጸዋል። እንደ አቶ ጸጋዬ ገለጻ የሥርዓቱ ዋና ዓላማዎች ሰነዶችን በቀላሉ ተደራሽ ማድረግ፣ ደህንነታቸውን ማረጋገጥ፣ የሕይወት ዑደታቸውን ማስተዳደር እና ፋይሎችን በተቀላጠፈ ሁኔታ በማደራጀት ቢሮክራሲያዊ መዘግየቶችን ማስወገድ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም የውይይት ማጠቃለያ እና የስራ አቅጣጫ በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ተሰጥቷል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት በማጠቃለያቸው ለውይይት የቀረቡት ሰንዶች የመንግሥት ግዥ ሥርዓት ወደ ላቀ የዲጂታል ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ፣ የመንግሥትን ግዥ ማዘመን ከውስጥ ሰነድ አያያዝ ማዘመን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለውና የሰነድ አያያዝን ማዘመን እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል። በመሆኑም ሁሉንም ስርዓቶች ወደ ሙሉ የትግበራ ሂደት መግባት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *