በግዥ ስርዓት ውስጥ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል የኤሌክትሮኒክስ መንግስት ግዥ ስርዓት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ተነገረ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ከፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ባለስልጣን ጋር በመተባበር ለተመረጡ ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ቅድመ ትግበራ ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የኤሌክትሮኒክስ መንግስት ግዥ ፕሮጀክት የአቅም ግንባታ አስተባባሪ አቶ ደበበ ማሞ እንዳሉት አሁን ላይ ሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች እና ከፍተኛ የመንግስት የትምህርት ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ መንግስት የግዥ ስርዓትን ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክስ መንግስት የግዥ ስርዓት ከሰው ንክኪ የፀዳና ወረቀት አልባ መሆኑ በዘርፉ ይስተዋል ለነበረው ችግር መፍትሔ ሆኗል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የግዥ ስርዓቱ ወጥ እንዲሆንና እንዲዘምን በተያዘው አቅጣጫ መሰረት የኤሌክትሮኒክስ መንግስት የግዥ ስርዓቱ በሁሉም ክልሎች ተግባራዊ እንዲደረግ የሚያስችል ስራ በተመረጡ ተቋማት ተጀምሯልም ብለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፋይናንስ ቢሮ የግዥ ንብረት አስተዳደር ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ማዲያ አልበሽር በበኩላቸው በክልሉ በተመረጡ 10 ተቋማት የሚተገበረው የኤሌክትሮኒክስ መንግስት የግዥ ስርዓት ባለፉት ዓመታት ከግልፀኝነት ማነስ፣ ከጊዜ ብክነትና ከብልሹ አሰራር ጋር ተያይዘው ይነሱ ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በተለይ ዘመኑ ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በመጠቀም የግዥ አሰራሮችን ዘመናዊ፣ ግልፅ፣ ፈጣንና ተጠያቂነትን በማስፈን የመንግስት ሀብትና ንብረት ለታለመለት ዓላማ ላይ እንዲውል ያስችላልም ብለዋል፡፡
የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ከፍተኛ የግዥ አማካሪ አቶ ከማል አብደላ እንዳሉት ደግሞ የኤሌክትሮኒክስ መንግስት የግዥ ስርዓት የመንግስት ሀብትና ንብረትን ለመቆጣጠር አስፈላጊነቱ ታምኖበት ከ2017 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አሳውቀዋል፡፡
በክልሉ ለትግበራው የተመረጡ ተቋማት በተያዘው በጀት ዓመት ወደ ሙሉ ትግበራ እንዲገቡ የሚያስችሉ ስራዎች በመሰራት ላይ ናቸውም ብለዋል፡፡
(#መረጃው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሚዲያ ነው)





0 Comments