በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ታትሞ ከተሰራጨው የኦዲት ተግባራት የተቀነጨበ

ጥያቄ፡ የኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ሥርዓት ምንድን ነው? ለምንስ አስፈለገ?
አቶ አዲስ:- የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (Electronic Government Procurement/ e-GP) ማለት ሁሉንም የመንግሥት ግዥ ሂደቶች በኤሌክትሮኒክ መንገድ የሚያከናውን የቴክኖሎጂ ሥርዓት ነው። ይህም ማለት የግዥ ሂደቱ ከግዥ ዕቅድ ዝግጅት ጀምሮ የጨረታ ማስታወቂያ፣ የተጫራቾች ምዝገባ፣ የጨረታ ግምገማ፣ የውል አስተዳደር እና ሪፖርት አያያዝ ድረስ ዲጂታል በሆነ መንገድ በአንድ ማዕከላዊ ሥርዓት ውስጥ ይከናወናሉ።
ዲጂታል ሥርዓቱ ያስፈለገው የወረቀት ሥርዓት ለጊዜ መጓተት፣ ለመረጃ መጥፋት፣ ለሙስና ተጋላጭነት እና ለውሳኔ አሰጣጥ አለመግለጽ ምክንያት ስለሚሆን ነው። የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ይህንን በመቀየር የግዥ ሥርዓቱን ዘመናዊ እና ቀልጣፋ አድርጎታል። ሌላው ጉዳይ ሀገራችን ዲጂታል ኢኮኖሚን በቁርጠኝነት እየተገበረች
የምትገኝ እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናን ከቴክኖሎጂ ጋር አጣምራ በትኩረት እየሠራች እንደሆነ ይታወቃል። ስለሆነም የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) የሀገራችን ዲጂታል ኢኮኖሚ በማገዝ ረገድ ያለው ሚና የጎላ ነው።
ጥያቄ፡ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት (e-GP System) ከሕጋዊነት ኦዲት ጋር እንዴት ይገናኛል?
አቶ አዲስ:- የሕጋዊነት ኦዲት ዋና ዓላማ የግዥ ሂደቶች ከሕግ እና ከመመሪያ ጋር ተጣጥመው መፈጸማቸውን ማረጋገጥ ነው። በዚህ ረገድ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት (e-GP System) ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትን እና ቅልጥፍናን በማረጋገጥ ከሕጋዊነት ኦዲት (Compliance Audit) ጋር በቀጥታ ይገናኛል።
የኦዲት አካላት እንደ አዋጅ፣ መመሪያ እና ደንቦች ያሉ የግዥ ሕጎች መከበራቸውን ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ትክክለኛ መረጃዎችን፣ የግብይት ሰነዶችን እና የውሳኔ ዱካዎችን (Audit Trails) ከሲስተሙ በቀላሉ ማግኘት ያስችላል። በመሆኑም ኦዲተሮች የጨረታ ማስታወቂያ መቼ እንደወጣ፣ ስንት ተጫራቾች እንደተሳተፉ፣ የግምገማ ሂደቱ እንዴት እንደተከናወነ እና ውሳኔው በምን መስፈርት እንደተሰጠ ወጪን፣ ጊዜና ጉልበትን ሳያባክኑ ባሉበት ሆነው በቀላሉ ማረጋገጥ ይችላሉ። ይህም የኦዲትን ሥራ የበለጠ ቀላል፣ ተዓማኒ እና ትክክለኛ ያደርገዋል።

0 Comments