በመመሪያዎች ላይ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

(ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በአዋጅ 1333/2016 የተሰጠውን ተግባርና ሀላፊነት ለመወጣት የአዋጅ ማስፈጸሚያ መመሪያዎችንና የአሰራር ስርዓቶችን ከማዘጋጀት ባለፈ መመሪያዎችንና የአሰራር ስርዓቶችን ተገልጋዩ ማህበረሰብ አውቆና ተረድቶ እንዲፈጽማቸው ለማስቻል ተከታታይ ስልጠናዎችን እየሰጠና ውይይቶችን እያካሄደ ይገኛል።
በዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከጥቅምት 19-21/2018 ዓ.ም ለፌዴራል ተቋማት የህግ፣ የስነ መግባር እና የውስጥ ኦዲት ሀላፊዎችና ባለሙያዎች በፌዴራል መንግስት የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017 እና በፌዴራል መንግስት የንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1095/2017 ላይ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።
በፌዴራል መንግስት የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017 ላይ ስልጠና የተሰጠው በኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ተጓዴ እና ወ/ሮ ወገኔ አይሸሽም ሲሆን አዲሱ መመሪያ ቀድሞ ከነበረው መመሪያ በብዙ መንገዶች የተለዬ መሆኑ ተብራርቷል። አቶ መላኩ በገለጻቸው በቀድሞ የግዥ መመሪያ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች ለአዲሱ የግዥ መመሪያ ዝግጅት ግብዓት ማድረግ እንደተቻለና መመሪያው የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፈተኛ ዋጋ እንዲያስገኝ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።
በሌላ በኩል በፌዴራል የመንግስት የንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1095/2017 ላይ ስልጠና የሰጡት በኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥና ንብረት እቅድና መረጃ ዴስክ ሀላፊ የሆኑት አቶ ዘበነ ገዛኸ ሲሆኑ አዲሱ የንብረት አስተዳደር መመሪያ ተለምዷዊ አሰራርን በማስቀረትና ዲጂታል አሰራርን በማስፈን በኩል ትልቅ ለውጥ የሚያሳይ መሆኑን አመላክተዋል። አቶ ዘበነ በማብራሪያቸው ንብረትን በእቅድ መምራት፣ ንብረትን በአግባቡ ይዞ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል ማድረግ፣ የንብረት አወጋገድን በአግባቡ ማከናወን እና በግንባታ ላይ ያሉ ንብረቶች የንብረት ስራ ክፍል ክትትል ማድረግ እንዲሚጠበቅበት መመሪያው እንደሚያስገነዝብና ሁሉም በየተሰጠው የስራ ሀላፊነት ልክ ንብረቶችን መያዝና መጠበቅ እንደሚገባው አብራርተዋል፡፡









0 Comments