“ልዩ አስተያየት ማለት ትኩረት ለሚሹ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት በውድድር ወቅት የሚሰጥ የተለየ ድጋፍ ማለት ነው”
ከመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያና አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ተጓዴ ጋር የተደረገ ቆይታ
በዮናስ ሀበሻ (የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ)
ታህሳስ 12/2018 ዓ.ም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የታተም
የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የተሰጠውን ተልዕኮ እና ርዕይ ለማስፈጸም እያከናወናቸው የሚገኙትን ተግባራት በዚህ ዓምድ እያቀረብን ማስነበባችን የሚታወስ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ የባለስልጣኑ የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያና አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ተጓዴን ልዩ አስተያየት ምን ማለት እንደሆነ፣ ዓላማው፣ አፈጸጸሙ እና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ጥያቄዎች በማንሳት የሰጡትን ምላሽ በሚከተለው መልኩ አቅርበናል፡፡
የልዩ አስተያየት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ቢገልጹልን?
አቶ መላኩ – በቅድሚያ በመንግስት የግዥ ህግ ማዕቀፍ ላይ በማሻሻያ እና በአዲስ መልክ እንዲካተቱ ከተደረጉ ድንጋጌዎች መካከል ልዩ አስተያየት አንዱ ነው፡፡ ቀደም ሲል በነበረው የህግ ማዕቀፍ ላይ የልዩ አስተያየት በተወሰነ ደረጃ የተቀመጠ ቢሆንም የመንግስትን ፖሊሲ ከመደገፍ፣ ልዩ ትኩረት የሚሹ አካላትን ከማበረታታት እንዲሁም ከአፈጻጸም አኳያ ውስንነት ያለበት መሆኑ ከግዥ ፈጻሚዎች፣ ከንግዱ ማህበረሰብ፣ ከህግ አውጪው፣ ከልማት አጋሮች እና ከሲቪክ ማህበራት ጋር በነበረ ውይይት ሲነሳ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም አዲስ በወጡ የግዥ የህግ ማዕቀፎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ከላይ የተጠቀሱትን ችግሮች በሚፈታ መልኩ ዝርዝር አፈጻጸም እንዲዘጋጅለት ተደርጓል፡፡
ወደ ጥያቄው ስመለስ ልዩ አስተያየት ማለት በመንግሥት የግዥ ሂደት ለሀገር ውስጥ ምርቶች፣ ለኢትዮጵያውያን ከምክር ውጭ የሆነ አገልግሎት ሰጪዎች፣ አማካሪዎች፣ ሥራ ተቋራጮች እና ልዩ ትኩረት ለሚሹ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት በውድድር ወቅት የሚሰጥ የተለየ ድጋፍ ነው፡፡
የልዩ አስተያየት ዓላማው ምንድነው ?
አቶ መላኩ – የልዩ አስተያየት ዓላማዎቹ በርካታ ቢሆኑም በዋናነት መንግስት የጀመረውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ዕውን ለማድረግ፣ የአምራች ዘርፉን ለማበረታታት፣ ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ የህብረተሰባችን ክፍሎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እና የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህል ማጎልበትን ዓላማ ባደረገ መልኩ የግዥ የህግ ማዕቀፎች ውስጥ ልዩ አስተያየት እንዲካተት ማድረግ ነው፡፡
የልዩ አስተያየት አፈጻጸም ምን ይመስላል ?
አቶ መላኩ –ልዩ አስተያየት በተመለከተ በቅድሚያ አዋጁ ላይ በግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016 የሰፈሩ ድንጋጌዎችን ማየት ያስፈልጋል በዚህ አዋጅ አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ በጨረታ ግምገማ ወቅት በኢትዮጵያ ለተመረቱ ዕቃዎች፣ ለኢትዮጵያውያን ከምክር ውጭ የሆነ አገልግሎት ሰጪዎች፣ አማካሪዎች እና ሥራ ተቋራጮች፤ በውጭ ሀገር ድርጅቶችና በሀገር በቀል ድርጅቶች መካከል ለሚመሠረት ጥምረት ወይም የሽርክና ወይም የእሽሙር ማህበር እና በማምረት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት፣ አካል ጉዳተኞች፣ የነጋዴ ሴቶች ማህበራት፣ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች ለሚያቀርቡ አካላት የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ስለሆነም አዋጁን ለማስፈጸም በወጣው የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017 ከአንቀጽ 26 ጀምሮ የልዩ አስተያት አፈጻጸምን በሚመለከት ዝርዝር አሠራሩን ያስቀመጠ ሲሆን የልዩ አስተያየቱን አይነት፣ መጠን እና ሊሟላ የሚገባው የታከለ እሴት መጠን በተወሰነ መልኩ ለማየት ብንሞክር፡-
ለመድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያዎች የሚደረግ ልዩ አስተያየት
| የተጨማሪ እሴት ምጣኔ | የልዩ አስተያየት መጠን |
| 20%- 35% | 20% |
| 36%- 50% | 21% |
| 51% -65% | 22% |
| 66%- 80% | 23.5% |
| 81% – 100% | 25% |
ለዕቃዎች የሚደረግ ልዩ አስተያየት
| የተጨማሪ እሴት መጣኔ | የልዩ አስተያየት መጠን |
| 20%- 35% | 10% |
| 36%- 50% | 11% |
| 51% -65% | 12% |
| 66%- 80% | 13.5% |
| 81% – 100% | 15% |
ሌላው ለግንባታ ሥራ እና ለምክር አገልግሎት ግዥዎች 7.5% እና ከምክር ውጭ የሆኑ አገልግሎት ግዥዎች 3%፣ ከሥራው ጠቅላላ ዋጋ ከ20 ከመቶ የማያንስ ዋጋ ያለውን ሥራ በንዑስ ተቋራጭነት ለጥቃቅንና አነስተኛ ማኅበራት ለመስጠት ግዴታ የገባ ከሆነ በጨረታው ለዋጋ ከተያዘው ነጥብ ተጨማሪ 2 በመቶ፣ በማምረት ሥራ ላይ ለተሰማሩ አካል ጉዳተኞች 3 ከመቶ፣ በማምረት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ነጋዴ ሴቶች ማህበራት 3 ከመቶ፣ በማምረት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት 3 ከመቶ፣ በውጭ ሀገር ድርጅቶች እና በአገር በቀል ድርጅቶች መካከል ለሚመሰረት ጥምረት ወይም የሽርክና ወይም የእሽሙር ማህበር 3.5 ከመቶ፣ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤትን ለማቅረብ የሚሳተፉ ተጫራቾች ከሌሎች የውጭ አገር እና የአገር ውስጥ ተጫራቾች ጋር በሚሳተፉበት ጊዜ 5 ከመቶ የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ ይሆናሉ ፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት በተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተቋማት ብቻ የሚሳተፉበት የግዥ አሠራር የተዘረጋ ሲሆን ይህም ከሰላሳ ሚልዮን ብር የማይበልጥ ዋጋ ያለው የግንባታ ሥራ የሥራ ዕድል የፈጠሩ ተቋማትን ብቻ አግባብነት ባለው የግዥ ዘዴ በማወዳደር የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እንዲያሠሩ የተዘረጋ አሠራር አለ፡፡ እንዲሁም ከአምስት ሚልዮን ብር የማይበልጥ ዋጋ ያላቸውን ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን፣ የእንጨትና የብረታ ብረት ውጤቶችን፣ ምግብ እና የምግብ ነክ ምርቶችን የሚያመርቱና የሚያቀርቡ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተቋማትን ብቻ አግባብነት ያለውን የግዥ ዘዴ ተጠቅመው ግዥ መፈጸም የሚችሉበት አሠራር የተዘረጋ ሲሆን በዚሁ አግባብ ተቋማት ግዥዎቻቸውን ሲፈጽሙ በግዥ ህጉ ላይ የተቀመጡ የልዩ አስተያየት ድንጋጌዎችን መሠረት በማድረግ እየፈጸሙ ይገኛል፡፡
የልዩ አስተያየቱ ተጠቃሚ ለመሆን ከንግዱ ማህበረሰብ ምን ይጠበቃል ?
አቶ መላኩ – በቅድሚያ የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ ለመሆን በመሥሪያ ቤቶች የተጠየቁ የቅድመ ግምገማ እና የቴክኒክ መስፈርቶች በተጫራቹ ተሟልተው መቅረብ ያለባቸው ሲሆን፣ የተጠየቁትን መስፈርቶች አሟልተው ወደ ፋይናንስ ግምገማ የገቡ ተጫራቾች በፋይናንስ ግምገማ ወቅት ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በግዥ ህጉ ላይ የተቀመጠውን የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ ለመሆን መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን ብንመለከት፡- መድኃኒት፣ የሕክምና መሣሪያዎች እና ዕቃዎችን ለማቅረብ የተወዳደሩ አቅራቢዎች የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ የሚሆኑት ጨረታ የወጣበትን ዕቃ ለማምረት ከወጣው ጠቅላላ ወጪ ላይ የተጨማሪ እሴት ምጣኔ በተመሰከረለት ኦዲተር በኢትዮጵያ ውስጥ የታከለ እሴት መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው የታከለ ዕሴት ማለት ከጠቅላላ ወጪ ላይ ከውጭ አገር ለሚመጡ ጥሬ ዕቃዎች እና ሌሎች አቅርቦቶች እንዲሁም ከውጭ አገር ለተገኘ አገልግሎት የተደረገ ወጪ ተቀንሶ የሚቀረው ወጪ ነው፡፡
ለኢትዮጵያውያን አገልግሎት ሰጪዎች፣ አማካሪዎች እና ሥራ ተቋራጮች ሲሆን፡-ድርጅቱ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የተቋቋመ እና ዋና መሥሪያ ቤቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ ከድርጅቱ አክሲዮን ወይም የካፒታል ድርሻ ከሃምሳ በመቶ በላይ በኢትዮጵያውያን የተያዘ ሲሆን፣ ከድርጅቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት መካከል ከ ሃምሳ በመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ከሆኑ እና ከድርጅቱ ቁልፍ ሠራተኞች መካከል ቢያንስ አርባ በመቶ ኢትዮጵያውያን ከሆኑ የልዩ አስተያየቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
ኢትዮጵያውያን አባል ለሆኑባቸው የሽርክና፣ የጥምረት ወይም የአሽሙር ማህበር የሚደረግ ልዩ አስተያየት በተመለከተ፡-ከሚፈጸመው የግንባታ ሥራ ወይም የምክር አገልግሎት ጠቅላላ መወዳደሪያ ዋጋ ውስጥ የሀገር በቀል ድርጅት ቢያንስ አርባ በመቶ መጠን የያዘ ከሆነ እና ከቁልፍ ሠራተኞች መካከል ቢያንስ አርባ በመቶ ኢትዮጵያውያን ከሆኑ የልዩ አስተያየቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡
በማምረት ሥራ ላይ ለተሰማሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት የልዩ አስተያየቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት፡-አግባብነት ባለው የአነስተኛና ጥቃቅን የሥራ ዕድል ፈጠራ ሕግ መሰረት የተቋቋሙ መሆን አለባቸው፤ ማህበራቱ ልዩ አስተያየት የሚደረግላቸው የራሳቸው የሆኑ የሥራ ውጤት ምርቶችን ለማቅረብ ብቻ ይሆናል፤ የሚወዳደሩበት የግዥ መጠን እስከ ብር አስር ሚሊዮን ብቻ ነው፤ ፈቃዳቸውን ለሌላ ሦስተኛ ወገን ያላስተላለፉ፣ በጥቃቅን ወይም በአነስተኛ ብቻ ተደራጅተው የቆዩ መሆኑን በጨረታ ማስከበሪያ እና በውል ማስከበሪያ ምትክ ማህበራቱን ካደራጃቸው የመንግስት ተቋም የሚሰጥ የጨረታ ማስከበሪያ የድጋፍ ደብዳቤ እና የውል ማስከበሪያ ደብዳቤ ማህበራቱ ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን የሚቀርበው የድጋፍ ደብዳቤ ዋስትና የተሰጠበትን የገንዘብ መጠን በመጥቀስ ማህበራቱን ባደራጃቸው መሥሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ የተፈረመ መሆን ይኖርበታል፡፡ ማህበራቱ የተቋቋሙበትን የሕጋዊነት ማስረጃ በማቅረብ የጨረታ ሰነድ ያለ ክፍያ በነፃ ይሠጣቸዋል፡፡
በማምረት ሥራ ላይ ለተሰማሩ አካል ጉዳተኞች ማህበራት የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ የሚሆኑት፡- በማህበር ተደራጅተው የማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ እና ምርታቸውን የሚያቀርቡ ማህበራት መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተቀጣሪ ሠራተኞችን ሳይጨምር የማህበሩ የአክሲዮን ባለቤትነት ድርሻ ቢያንስ ሰባ በመቶ በአካል ጉዳተኞች የተያዘ መሆን አለበት፡፡ ተገቢው የአካል ጉዳተኝነት ማስረጃ ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም መቅረብ አለበት፡፡
በማምረት ሥራ ላይ ለተሰማሩ የነጋዴ ሴቶች ማህበራት የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ የሚሆኑት፡-በማህበር ተደራጅተው የማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ እና ምርታቸውን የሚያቀርቡ ማህበራት መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ተቀጣሪ ሠራተኞችን ሳይጨምር የማህበሩ የአክሲዮን ባለቤትነት ድርሻ ቢያንስ ሰባ በመቶ በሴት ማህበር የተያዘ መሆን አለበት፡፡ በነጋዴ ሴቶች ማህበር የተደራጁ ስለመሆናቸው ማስረጃ ከሚመለከተው አካል መቅረብ አለባቸው፡፡
ለቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች የሚያቀርቡ የልዩ አስተያየትተጠቃሚ የሚሆኑት፡-የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቱ ለአካባቢ ጥበቃ ወይም ለማህበራዊ ልማት አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆን ይኖርበታል፤ ወይም የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቱ ግዥ ከተከናወነ በኋላ የቴክኖሎጂውን ዘላቂነት ያለው አጠቃቀም ማሳየት አለበት፤ ወይም የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቱ በመንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው ዘርፎች የስራ እድል ፈጠራ እና የክህሎት ዕድገትን የሚያበረታታ መሆን አለበት፤ ወይም የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቱ ከውጭ አገር የሚመጡ ዕቃዎችን ለመተካት የሚደግፉ እና ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ጥገኝነትን የሚቀንስ ቴክኖሎጂ መሆን አለበት፤ ወይም የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቱ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ እና የወጪ ንግድ ብዝሃነትን የሚያበረታታ መሆን አለበት፤ ወይም የቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቱ ለተሻለ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥ እና የዜጎች ተሳትፎን የሚደግፍ መሆን አለበት፡፡
ከላይ የተገለጹት ቅድመ ሁኔታዎች እንደተጠበቁ ሆነው በማምረት ሥራ ላይ የተሰማሩ የጥቃቅንና አነስተኛ፣ የሴቶች ነጋዴ ማህበራት እና የአካል ጉዳተኞች ማህበራት ብቻ እርስ በርሳቸው በጨረታ በሚገናኙበት ጊዜ በመመሪያ ከተፈቀደው ልዩ አስተያየት ውጪ እኩል ነጥብ ቢያመጡ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለሴቶች፣ ለጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት እንደ ቅደም ተከተላቸው ቅድሚያ የሚሰጥ ሆኖ በውድድሩ ተመሳሳይ ማህበራት እኩል ነጥብ ቢያመጡ በዕጣ የሚለዩ ይሆናል፡፡
ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እነዚህ የልዩ አስተያየት በግዥ ህጉ ላይ በተቀመጠው መሠረት መተግበራቸውን የሚያረጋግጥበት እና የሚከታተልበት አሠራር አለ ?
አቶ መላኩ – እንደሚታወቀው ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከተቋቋመበት ዋና ዓላማዎች መካከል የመንግሥት ግዥ አፈፃፀም አዋጁን እና አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን መመሪያ ላይ የሠፈሩ ድንጋጌዎችን ተከትለው መሥሪያ ቤቶች ግዥ መፈጸማቸውን የመከታተል እና የመቆጣጠር ኃላፊነት አንዱ ነው፡፡
በዚህ ረገድ በመሥሪያ ቤታችን የኦዲትና ክትትል የሥራ ክፍል በኩል ተቋማት ኦዲት ሲደረጉ በኦዲት ቼክ ሊስት ውስጥ ከተካተቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ውስጥ የልዩ አስተያት አፈጻጸም ዋናው ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ በግዥ ሂደት ላይ የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚገባቸው አቅራቢዎች/ሥራ ተቋራጮች/ እና አማካሪዎች የልዩ አስተያየት ተጠቃሚ መሆን አለመቻላቸውን ካረጋገጡ ወይም በደል ደርሶብኛል ብለው ካመኑ በየደረጃው የግዥ ህጉን ተከትለው አቤቱታቸውን ለግዥ ፈጻሚው የበላይ ኃላፊ ያቀርባሉ፡፡እንዲሁም ይግባኛቸውን ለቦርድ የሚያቀርቡበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እነዚህን የግዥ ህግ ድንጋጌዎች በተሟላ መልኩ ተቋማት እንዲተገብሩ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ሲሆን ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
0 Comments