Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

News

ባለስልጣኑየኮንትራትማኔጅመንትአቅምንለማጠናከርያለመስልጠና እየሰጠ ነው።

(ሀምሌ 10/2018 ዓ.ም)፣ የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በገጠር ትሥር ኮኔክቲቪቲ (Rural Connectivity) ፕሮግራም ማዕቀፍ ውስጥ የሚፈጸሙ የኮንትራት ፕሮጀክቶችን በተሻለ ብቃት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ለመምራት የሚያስችል ሀገራዊ የኮንትራት ማኔጅመንት ስልጠና መድረክ ከፍቷል።

የስልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት ይህ መድረክ በክልል መንገድ ዘርፍ፣ በፋይናንስ ተቋማት እና በክልል ግዥ ባለስልጣናት መካከል የጋራ ግንዛቤን ለማጠናከርና በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ የሚታዩ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት ያለመ መሆኑን አመላክተዋል።

ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ በንግግራቸው የገጠር ትስስር (Rural Connectivity) ፕሮግራም የገጠር ማህበረሰቡን ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አገልግሎቶች ጋር በማገናኘት የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ወሳኝ ሀገራዊ ፕሮግራም መሆኑን ጠቅሰዋል። የገጠር መንገዶችና የመጓጓዣ መሠረተ ልማቶች የገበያ ተደራሽነትን፣ የግብርና ምርትን፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎትን እንዲሁም የስራ ዕድል ፈጠራን የሚያፋጥኑ መሠረታዊ የልማት መሣሪያዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

“እያንዳንዱ የሚገነባ ኪሎ ሜትር መንገድ በዜጎቻችን የኑሮ ጥራት ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ አለው” ያሉት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የፕሮጀክቶች ስኬት ግን በጀት በመመደብ ብቻ እንደማይረጋገጥ ይልቁንም ጥራት ያለው የግዥ ሂደት፣ ውጤታማ የኮንትራት አስተዳደር፣ ወቅታዊ ክትትል፣ ትክክለኛ የፋይናንስ አያያዝ እና ጠንካራ የተቋማት ቅንጅት በአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዛሬ በአለም አቀፍ ደረጃ የመንግስት ግዥ ዓላማ ከዝቅተኛ ዋጋ አሰራር ወጥቶ ወደ “Value for Money” (ለገንዘብ ተገቢውን ዋጋ ማግኘት)፣ ዘላቂነት፣ እና የህይወት ዑደት ወጪ ትንተና (Life Cycle Cost Analysis) ላይ ትኩረት እያደረገ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል። ባለስልጣኑም ይህንን መሠረት በማድረግ የግዥ ሥርዓቱ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተወዳዳሪና ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን የህግ ማዕቀፎችንና የቴክኖሎጂ አሰራሮችን በመዘርጋት የተቋማትን አቅም ለመገንባት በስፋት እየሰራ ይገኛል።

በውይይቱ በኮንትራት ማኔጅመንት ውስጥ የለውጥ ትዕዛዞችን (Variation Orders) በአግባቡ ማስተዳደር፣ የጊዜ ማራዘሚያ ጉዳዮችን በአግባቡ መመርመር እና ክፍያዎችን በግልጽነት መፈጸም የፕሮጀክቶችን ስኬት እንደሚወስኑ የተገለጸ ሲሆን ሊያጋጥሙ የሚችሉ የዋጋ መለዋወጥ፣ የአየር ጸባይና የቴክኒክ ስጋቶችን (Risks) ቀድሞ በመለየት የጥንቃቄ ስልቶችን ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።

“የተከልነው ችግኝ ብቻ ሳይሆን የነገ ተስፋችን ጭምር ነው” — ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ

(ሐምሌ 02 ቀን 2018 ዓ.ም)፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን «የነገ ተስፋን በጋራ እንትከል» በሚል መሪ ቃል የተጀመረውን ብሔራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሯል። በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 በሚገኘው በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ (AASTU) ቅጥር ግቢ ውስጥ በተከናወነው በዚህ ንቅናቄ ከ1,000 (አንድ ሺህ) በላይ የፍራፍሬ ችግኞች ተተክለዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የባለሥልጣኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ ሠራተኞች፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማና የወረዳ 09 አመራሮች እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

በዕለቱ የተከላ መርሃ ግብሩን በይፋ የከፈቱትና ለተሳታፊዎች መልዕክት ያስተላለፉት የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በንግግራቸው ዛሬ መሬት ላይ ያረፈው ችግኝ ብቻ ሳይሆን የነገው ትውልድ ተስፋ ጭምር መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም የተከላ መርሃ ግብሩ ነገ አገርን የሚረከብ ትውልድ በሚገነባበት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ መከናወኑ ልዩ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ይህ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ አካባቢን ከአረንጓዴ ማልበስ ባለፈ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ስነ-ምህዳርን ለማስተካከል እጅግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ፦

“ይህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement) አካልና ስትራቴጂያዊ መገለጫ ሲሆን፣ በቀጥታም ከባለሥልጣኑ ተልዕኮና የወደፊት አቅጣጫዎች ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ክቡር ዶ/ር ደረጄ እንግዳ በበኩላቸው ባለሥልጣኑ ተቋማቸውን መርጦ አረንጓዴ አሻራውን በማሳረፉ ምስጋና አቅርበው ዛሬ የተተከሉት ከ1,000 በላይ ችግኞች በልዩ ሁኔታ እንክብካቤ ተደርጎላቸው እንዲጸድቁና ምርታማ እንዲሆኑ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ኃላፊነት እንደሚወጣና ክትትል እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እና የወረዳ 09 አመራሮችም፣ እንዲህ አይነት ማህበረሰባዊና አካባቢያዊ ፋይዳ ያላቸውን ብሔራዊ ጥሪዎች ተቋማት በአካባቢያቸው መጥተው ሲያከናውኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ለማድረግ ምንጊዜም ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የዕለቱ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የባለሥልጣኑ አመራሮችና ሠራተኞች ያሳዩበት ከፍተኛ ተነሳሽነትና የወንድማማችነት ስሜት በታየበት መልኩ በስኬት ተጠናቋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት በባለስልጣኑ የአሰራር ስርዓትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የመስክ ምልከታና ግምገማ አካሄደ

(ሰኔ 27/2018 ዓ.ም)፣ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን የአሰራር ስርዓት እና የዲጂታልና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ለመገምገም የሚያስችለውን የመስክ ምልከታና የሰነድ ምርመራ አካሂዷል።

የግምገማ መድረኩን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሚኒሊክ ሳሙኤል በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር የከፈቱ ሲሆን፣ ባለስልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራት፣ ተደራሽነትና ቅልጥፍና ይበልጥ ለማዘመን በርካታ ስትራቴጂካዊና ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን በትጋት እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። አያይዘውም የጥራት ሽልማት ድርጅቱ የገምጋሚ ኮሚቴ አባላት የሚሰጧቸው ገንቢ አስተያየቶችና ግብረ-መልሶች የተቋሙን የሪፎርም ጉዞ ይበልጥ ለማቀጣጠልና ለወደፊት ስራዎች እንደ ትልቅ መስፈንጠሪያ (Springboard) ሆነው እንደሚያገለግሉ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ በበኩላቸው፤ ባለስልጣኑ የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍናን ለመጨመርና አሰራሩን ለማዘመን (በተለይም በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን) ማከናወኑ የሚታወቅና ለሽልማት ድርጅቱም በሰነድ ያሳወቀ መሆኑን አንስተዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ የተከናወኑ ተስፋ ሰጪ ስራዎች ተቋማዊ ስርዓት የተበጀላቸው፣ ቀጣይነት ያላቸውና መሬት ላይ በግልጽ የሚታዩ መሆናቸውን በጥራት ሽልማት ገምጋሚ ኮሚቴው ማረጋገጥ እንደሚገባና ዋናው የሂደቱ ዓላማም ይሄው መሆኑን አስረድተዋል።

የጥራት ሽልማት ኮሚቴ አባላትም ባለስልጣኑ በተለያዩ ቁልፍ የተቋማዊ ብቃት መስፈርቶች ላይ ያለውን ልምድና አደረጃጀት በጥልቀት መዝነዋል። በተለይም የአሰራር ስርዓት ግንባታና ተቋማዊ ባህል፣ የውስጥና የውጭ ቅንጅታዊ አሰራር እንዲሁም ተግባቦት (Communications)፣ የሰራተኞች አያያዝ፣ የስራ አካባቢ ምቹነትና የማበረታቻ (ማትጊያ) ስርዓቶች፣ የተገልጋይ አያያዝ፣ ቅሬታ አፈታትና የደንበኞች ግንኙነት፣ የማህበራዊ ኃላፊነት (CSR) አፈጻጸም እና መሰል መመዘኛዎች ላይ ትኩረት አድርገዋል።

ከመስክ ምልከታው በኋላ ገምጋሚ ኮሚቴ ምልከታውን ያቀረበ ሲሆን የመስክ ምልከታና የባለሙያዎች ግምገማ ከውድድሩና ከጥራት ሽልማቱ ባለፈ ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት የያዘውን ዘመናዊ ጥራትና ቅልጥፍናን መሰረት ያደረገ የሪፎርም ጉዞ የሚያጠናክርና ለተቋሙ ቀጣይ እድገት ትልቅ ተጨማሪ እሴት (Value Addition) የሚፈጥር መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ገልጸዋልል።

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ::

(ሰኔ 26/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶች፣ የንብረት ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም የተሸከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ሥራ አስፈጻሚዎች እን ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በኢ-ፍሊት (e-Fleet Management System) ትግበራ እና በመንግስት ንብረት አወጋገድ አፈጻጸም ዙሪያ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

 

በመድረኩን የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የውይይት መድረኩ በሀገራችን የመንግስት ንብረትና የተሸከርካሪ አስተዳደር ሥርዓትን የበለጠ ቀልጣፋ፣ ግልጽ፣ ተጠያቂ እና ውጤታማ ለማድረግ በሚደረገው የለውጥ ጉዞ ውስጥ አንዱ አስፈላጊ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል። ዋና ዳይሪክተሯ አያይዘውም የንብረት አያያዝና አወጋገድ ስርዓቱም ከባቢን በማይበክል እና መልሶ መጠቀምን በሚያበረታታ መልኩ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።

የንብረት አያያዝንና አወጋገድን አፈጻጸምን አስመልክቶ ገላጻ ያቀረቡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያ እና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላክ ተጓዴ በበኩላቸው የመንግስት ተቋማት ያሉባቸውን የአፈጻጸም ክፍተቶች መለየት ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ አገልግሎት የማይሰጡና የተከማቹ ንብረቶችን በተገቢው ሒደትና ፍጥነት ማስወገድ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲሁም የንብረት አያያዝንና አወጋገድን ለማሻሻል እየተወሰዱ ስላሉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን አብራርተዋል።

አቶ መላኩ በማብራሪያቸው አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶች በወቅቱ ካልተወገዱ የማከማቻ ወጪ እንደሚያስከትሉ፣ የንብረት መዝገቦችን እንደሚያዛቡ፣ የሥራ ቦታዎችን እንደሚያጨናንቁ እና የሙስና ተጋላጭነትን የሚጨምሩ በመሆናቸው በሕግና በመመሪያዎች መሠረት መፈጸም እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

በሌላ በኩል የኢ-ፍሊት (e-Fleet) ሥርዓት አጠቃቀምንና ተያያዥ አፈጻጸሞችን በተመለከተ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP Project) ማናጀር አቶ ያፌት መኮንን ዝርዝር ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ሥርዓቱ በመንግስት ተሸከርካሪዎች አስተዳደር ውስጥ ግልጽነትን ለማሳደግ፣ ወጪን ለመቆጣጠር እና ውሳኔዎችን በመረጃ ላይ ተመስርተው እንዲወሰኑ ለማድረግ የተዘረጋ መሆኑ ተገልጿል።

ከቀረቡት ገለጻዎች በኋላ ከተሳታፊ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ለቀረቡት ጥያቂዎችና አስተያየቶች የማጠቃለያ ማብራሪያ የሰጡት የመንግስት ሀብት የህዝብ ሀብት በመሆኑ በአግባቡ መጠቀምና መጠበቅ የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን በቀጣይም ተቋማቱ የኢ-ፍሊት ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀሙ፣ መረጃዎችን ወቅታዊ እንዲያደርጉ፣ የንብረት አወጋገድ ሂደቶችን በወቅቱ እንዲያስፈጽሙ እና የአመራር ክትትልን እንዲያጠናክሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በዚሁም ተጠያቂና ዘመናዊ የንብረት አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት በጋራ ለመስራት መግባባት ላይ በመደረስ ውይይቱ በስኬት ተጠናቋል።