Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

News

ባለስልጣኑ የፌደራልመንግስትግዥናንብረትየህጋዊነት ኦዲት ማንዋል ተግባር ላይ እንዲውል ወሰነ።

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር  1333/2016 የተሰጠውን ሀላፊነት ለመወጣት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። በተለይም አዳዲስ መመሪያዎች በገንዘብ ሚኒስቴር ወጥተው እንዲተገበሩ በማድረግ ደረጃ ከፍተኛ ሚና የተጫወተ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌሎች ማኑዋሎችንና የአሰራር ስርዓቶችን በመቅረጽ ወደ ስራ አስገብቷል።

ባለስልጣኑ በቅርብ አጽድቆ ወደ ተግባር እንዲገቡ ከአደረጋቸው ማኑዋሎች አንዱ የፌደራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የህጋዊነት ኦዲት ማንዋል ይገኝበታል።

ሰነዱ ምን ጉዳዮችን ይዟል?

ይህ ሰነድ በአምስት ክፍሎች እና በ82 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን የግዥና ንብረት አስተዳደር ኦዲት አጠቃላይ መግለጫ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኦዲት ዓላማዎች፣ ግቦች፣ ተግባራት፣ መርሆዎች እና እሳቤዎች፣  የተሳታፊ አካላት ስልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነትየግዥና ንብረት ኦዲት ክንውን ዑደት እና የኦዲት ማከናወኛ ሰነዶች በአባሪነት አካትቷል።

በመጀመሪያው ክፍል የመንግስት ግዥና ንብረት ኦዲት ፋይዳ፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኦዲት ባለድርሻ አካላት እና በኦዲት ስራ ወቅት ሊደረጉ የማይገቡ ተግባራት በስፋት ተብራርተዋል።

በሁለተኛው ክፍል በተለይም ኦዲት ዓላማዎች በግልጽ የተብራሩ ሲሆን የመንግስት የግዥና ንብረት የሕግ ማዕቀፎችን ተከትሎ የተፈጸመ መሆኑን ማረጋገጥ፣ ገንዘብ ሊያስገኝ የሚገባውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ (Value for Money) ማስገኘቱን ማረጋገጥ፣ ሙስና፣ ብልሹ አሰራር እና የመልካም አስተዳደር ችግርን መከላከልና ማጋለጥ፣  ግልጸኝነትና ፍትሃዊነት ውድድር መኖሩን ማረጋገጥ፣ የመንግስት ንብረትን መጠበቅ፣ ተጠያቂነት መኖሩን ማረጋገጥ፣ የግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር ሥራዎች እንዲሻሻሉ እገዛ ማድረግ የሚሉ አበይት ጉዳዮችን የያዘ ነው።

በዚህ ክፍል ከላይ ከተገለጹት በተጨማሪ የኦዲት ግቦች፣ ኦዲቱ የሚያካትታቸው ተግባራት፣ የኦዲት መርሆዎች እና እሳቤዎች በተለይም ገለልተኛነት (Independence)፣ የግዥና ንብረት አስተዳደር ህግና ዓለም አቀፍ የኦዲት ስታንዳርድ መከተል (Compliance with Laws & Standards)፣ ሙያዊ ስነ-ምግባር /Professional Ethics/፣ የኦዲት የሥራ ማህደሮች (Audit Working Papers) እና ተያያዥ ጉዳዮች በስፋት ተብራርተዋል።

በሞጁሉ ሦስተኛው ክፍል ስልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነት የያዘ ሲሆን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን፣ የኦዲት ተደራጊ ባለበጀት መ/ቤቶች፣ የግዥና ንብረት ኦዲት የሥራ ክፍል የኦዲት ባለሙያዎች ስልጣን፣ ተግባርና ሀላፊነትን ይዟል።

አራተኛው የሞጁሉ ክፍል የግዥና ንብረት ኦዲት ክንውን ዑደትን የያዘ ሲሆን የኦዲት ቅድመ ዝግጅት፣ የህጋዊነት ኦዲት ክንውን፣ የኦዲት ሪፖርት ዝግጅት፣ ቁጥጥር እና ክትትል አካትቷል።

የመጨረሻው የሞጁሉ ክፍል የኦዲት ማከናወኛ ሰነዶች የያዘ ሲሆን የተተመነውን ሰዓት ሥራ ላይ ከዋለው ሰዓት ጋር ማነፃፀሪያ፣ የሙያ ሥነ-ምግባር መከታተያ ቅጽ፣ የኦዲተሮች የቡድን ብቃት ስብጥርን ያሚያሳይ ቅጽ፣ የኦዲት የሥራ ስምምነት ደብዳቤ እና ተያያዥነት ያላቸውን ሰነዶች ይዟል።

ለበለጠ መረጃ፤

ድረ ገጽ፡ https://www.ppa.gov.et/

https://elearning.ppa.gov.et

ፌስቡክ፡ Public Procurement and Property Authority

ቴሌግራም፡ Public Procurement and Property Authority/የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣንና የድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር የመግባቢያ የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ።

(ጥር 14/2018 ዓ.ም)፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍናን ለማሳደግና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያገኝ ለማስቻል እየተገበራቸው ከሚገኙ የዲጂታል ስራዎች አንዱ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP system) ስርዓት ነው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን ስርዓት በሁሉም የፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲተገበር ያስቻለ ሲሆን ቀድመው የተገበሩትን የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች እንዲተገበር ለማስቻል ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል።

ባለስልጣኑ ተደራሽነትን ለማስፋትና በሁሉም ክልሎች እንዲተገበር ለማድረግ በሰራው ስራ የድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር ጋር የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP system) መተግበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት የድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሀላፊ ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ እና የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ናቸው። በፌርማው ስነ- ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ እንደገለጹት የዲጂታል ኢትዮጲያን ጉዞ ለማፋጠን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP system) ስርዓት ከፍተኛ አስተዋፆ እንዳለው አመላክተዋል። ክቡር አቶ ሀርቢ ቡህ በንግግራቸው የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት ብልሹ አሰራርን በመቀነስ፣ ወጪንና ጊዜን በመቆጠብ ለአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍና የሚሰጠው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ በትኩረት የሚሰራበት ይሆናል ብለዋል።

በሌላ በኩል የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ባለስልጣኑ የግዥ ሂድቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት አክለውም የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ ተደራሽነትን በማስፋት፣ አሳታፊነትን በመጨመር፣ ወጪን በመቀነስ እና ግልጸኝነትን በማስፈን ረገድ ያለው ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች እንዲተገብሩት የማማከር፣ የማሰልጠንና የግዥ ህጎቻቸውን ከፌዴራሉ የግዥ ህግ ጋር የተቀራረበ እንዲሆን ለማስቻል ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም አመላክተዋል።

በእለቱ ከመግባቢያ ሰነዱ መፈረም በተጨማሪ የባለስልጣኑ አመራርና ሰራተኞች በድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮች ጋር ውይይት አካሄደ።

ጥር 07/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ቅልጥፍና ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት እና ከተገልጋዩ ማህበረሰብ ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይትና ምክክር እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ዛሬ ከመንግስት ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ ከግዥና ንብረት ዳይሬክተሮችና ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት የመንግስት ትልቁ በጀት ለግዥ አገለግሎት የሚውል በመሆኑ ይህን በጀት በስርዓት መምራትና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ትልቅ ሀግራዊ ሚናን እየተወጣ የሚገኝና ውጤታማነቱን ለማስቀጠል ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብልከዋል።

በሌላ በኩል ለውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ቅልጥፍና ለመጨመር አገልግሎቶችን በሙሉ ዲጂታላይዝ እያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመንና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማስቻል የህግ ማዕቀፎችን መከለስና ተግባራዊ ማድረግ መቻሉንም አመላክተዋል።

 ዋና ዳይሬክተሯ በገለጻቸው የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ሁሉንም የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጨምሮ በሁሉም የፌዴራል የመንግስት ተቋማት ከመተግበር አልፎ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መተግበር መቻሉን ያብራሩ ሲሆን ይህም ስርዓቱ በውጤታማነት እየቀጠለ እንዳለ የሚያመላክት መሆኑን አብራርተዋል። አክለውም ሁሉም ክልሎች ስርዓቱን እንዲተገብሩት ለማስቻል እየተሰራ እንዳለና አብዛኞቹ ክልሎች የግዥና ንብረት ህጎቻቸውን ከፌዴራሉ የግዥና ንብረት ህግ ጋር የማጣጣም ስራ እየሰሩ እንደሆነ ተብራርቷል።

ባለስልጣኑ ከመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP System) በተጨማሪ የተሽከርካሪ ስምሪትና ነዳጅ ቁጥጥር (e- Fleet Management System)፣ ዲጂታል ደብዳቤ መላላኪያ (Letter Management System)፣ ዲጂታል አስተያየትና ጥቆማ መስጫ (Digital suggestion box) እና የመሳሰሉት ስራዎች ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ በማድረግ አገልግሎት ላይ እንደዋሉ ተገልጿል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው ከአነሷቸው ጉዳዮች አንዱ ተቋማዊ የሪፎርም ስራ ሲሆን የሪፎርም ስራዎች የተቋሙን ራዕይ እና ተልዕኮ ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውና የሪፎርም ስራዎችም በውጤታማነት እየተከናወኑ እንዳሉ አብራርተዋል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትንና ሌሎች የአሰራር ስርዓቶችን በውጤታማነት ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎችና  አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በዋና ዳይሬክተሯ እና ሌሎች የባለስልጣኑ የስራ ሀላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄደ።

(ጥር 05/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ቅልጥፍና ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት እና ከተገልጋዩ ማህበረሰብ ጋር ቀጣይነት ያለው ውይይትና ምክክር እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ዛሬ ከፌዴራል የመንግስት ተቋማት ሀላፊዎች፣ ከግዥ ዳይሬክተሮችና ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂዷል።

ውይይቱን በንግግር የከፈቱት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ አህመድ ሽዴ እንደገለጹት የመንግስት ትልቁ በጀት ለግዥ አገለግሎት የሚውል በመሆኑ ይህን በጀት በስርዓት መምራትና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ትልቅ ሀግራዊ ሚናን እየተወጣ የሚገኝና ውጤታማነቱን ለማስቀጠል ላለፉት ስድስት ወራት ማሻሻያዎች ሲደረጉ እንደቆዩ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ለውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ቅልጥፍና ለመጨመር ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም የአሰራር ስርዓቱን ለማዘመንና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማስቻል የህግ ማዕቀፎችን ከመከለስ ጀምሮ ተጨባጭ ስራዎች መሰራታቸውን አመላክተዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ ገለጻ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ በሁሉም የፌዴራል ተቋማት ከመተግበር አልፎ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር እና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መተግበር መቻሉ ስርዓቱ በውጤታማነት እየቀጠለ እንዳለ የሚያመላክት መሆኑን አብራርተዋል። በገለጻው ሁሉም ክልሎች ስርዓቱን እንዲተገብሩት ለማስቻል እየተሰራ እንዳለም ተብራርቷል። ባለስልጣኑ ከመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP System) በተጨማሪ የተሽከርካሪ ስምሪትና ነዳጅ ቁጥጥር (e- Fleet Management)፣ ዲጂታል ደብዳቤ መላላኪያ (Letter Management)፣ ዲጂታል አስተያየትና ጥቆማ መስጫ (Digital suggestion box) እና የመሳሰሉት ስራዎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ላይ እንደዋሉ ተገልጿል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው ከአነሷቸው ጉዳዮች አንዱ ተቋማዊ የሪፎርም ስራ ሲሆን የሪፎርም ስራዎች የተቋሙን ራዕይ እና ተልዕኮ ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንዳላቸውና የሪፎርም ስራዎችም በውጤታማነት እየተከናወኑ እንዳሉ አብራርተዋል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትንና ሌሎች የአሰራር ስርዓቶችን በውጤታማነት ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በዋና ዳይሬክተሯ እና ሌሎች የባለስልጣኑ የስራ ሀላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።