Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

News

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የሴቶችን ቀን በደማቅ ሁኔታ አከበረ።

*******************************************************

(መጋቢት 02/2018 ዓ.ም)፤  የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ ጊዜ “ለማግኘት መስጠት” በሀገራችን ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ “50 ዓመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ የሚገኘውን የሴቶች ቀን በደማቅ ሁኔታ አክብሯል።

በዓሉ በፓናል ውይይት እና በስልጥና የተከበረ ሲሆን እለቱን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በዓሉ ታስቦ የሚውል ብቻ ሳይሆን የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማጉላት እንደሚገባ አሳስበው አሁን ላይ የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሁሉም ዘርፍ እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም ሴቶች ድርብ ሀላፊነት ያለባቸው መሆኑንና ሴቶች ላይ መስራት ትውልድን ማስቀጠል መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በእለቱ ከበዓሉ ባለፈ በስሜታዊ ብስለት (Emotional intelligence) ላይ ለሴቶች ፎረም አባላት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ ስልጠናውን የሰጡት አቶ አራጋው ሲሳይ እንደገለጹት የስኬት ቁልፉ ምስጢር ስሜታዊ ብስለት መሆኑንና በተለይም ራስን ማወቅ፣ ማህበራሰብን/ከባቢን ማወቅ፣ ራስን መግዛት እና ግንኙነትን ማዳበር የስኬት ምንጮች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

ከበዓሉ በተጨማሪ ባለስልጣኑ በጡረታ የተሰናበቱ ሦስት ባለሙያዎችንም በክብር ሸኝቷል።

የመንግስት ኤሌክትሮኒክስ የግዥ ስርዓት ብልሹ አሠራርን የሚቀንስ እና ቀልጣፋ የግዥ ሂደትን ለመተግበር የሚያስችል ነው፡፡ አብዱ ሁሴን (ዶ/ር)

(የካቲት 25 ቀን 2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥ ስርዓቱን በማዘመንና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚገባውን ዋጋ እንዲያገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን ሁሉንም የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በሁሉም የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ከመተግበር ባለፈ ከተማ መስተዳደሮችና ክልሎችም እንዲተገብሩት እያደረገ ይገኛል፡፡

ባለስልጣኑ አስቀድመው የጀመሩትን አዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር፣ ከሶማሊ ክልል፣ ከሀረሪ ክልል፣ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ከመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ከሌሎችም ክልሎች ጋር ስርዓቱ መተግበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መግባባት የተደረሰ ሲሆን ዛሬ ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በዉይይት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ/ር) እንደገለጹት የኤሌክትሮኒክስ የመንግስት የግዥ ስርዓትን (e-GP System) መተግበር ዘመናዊ አሠራርን እንድንከተል ከማስቻሉም በላይ፣ ብልሹ አሰራርን የሚቀንስ እና ቀልጣፋ የግዥ ሂደትን ለመተግበር የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ርዕስ መስተዳደሩ አክለዉም የመንግስት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓርትን ለመተግበር ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንና በክልሉ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች እንዲተገበር ለማስቻል ድጋፍ የሚሰጥና በቅርበት ክትትል የሚደረግ መሆኑን ገልፃዋል፡፡

በሌላ በኩል የመንግስት ኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓት ምንነት፤ አላማዎችና የአተገባበር ሂደትን በሚመለከት የውይይት ሰነድ ያቀረቡት የኤፌድሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ በበኩላቸዉ ግዥን በኤሌክትሮኒክ ዘዴ መፈጸም ዉድድርንና እኩል እድልን የሚፈጥር፣ ገንዘብ የሚያስገኘዉን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስገኝ፣ የመንግስት የግዥ ህግ እንዲከበር የሚያስችሉ ዓላማዎችን ያነገበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ክብርት ወ/ሮ መሰረት አክለዉም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ የግዥ ዘዴ የግዥ ስራን በማቀላጠፍ፣ የሰነድ ማጭበርበርን በማስቀረት እና በግዥ ሂደት የተጠያቂነት ስርዓትን በማስፈን በኩል የላቀ ፋይዳ ያለዉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን በበኩላቸዉ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓትን ለመተግበር የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲሰሩ የቆዩ መሆኑን ገልጸዉ በቀጣይ በክልሉ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተዉ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ባለስልጣኑእያከናወናቸውየሚገኙትየሪፎርምሥራዎችበባለስልጣኑየአገልግሎትአሰጣጥጥራትናቅልጥፍናላይያመጡትተጨባጭለውጥአለብለውያምናሉ? ቢያብራሩልን።

አቶ ዳንኤል ፦ በሚገባ አምናለሁ፡፡ የሪፎርም ሥራዎች በባለስልጣኑ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍና ላይ ተጨባጭ ለዉጥ አምጥተዋል ስል ቀደም ሲል ለሙያዊ ምክር፣ ለስልጠና ጥያቄዎች፣ ለቴክኒካዊ ድጋፍ በተለይ ኢጂፒ አጠቃቀም ላይ ወደ ተቋማችን የሚመጡ ተቋማትም ሆነ የንግዱ ማህበረሰብ ማናቸዉንም አገልግሎቶች ባሉበት ሆነዉ በተዘረጋዉ ዲጅታል አሠራር አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ሊወጣ የሚችለዉን የጊዜ፣ የጉልበት፣ እና የገንዘብ ወጪ ማስቀረት ተችሏል፡፡

በተጨማሪም ኤሌክትሮኒክ ትምህርትን በመጠቀም የስልጠና እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች በመከናወናቸዉ ተገልጋዮች ባሉበት ሆነዉ ተቋሙን እንዲያዉቁትና ተቋሙ የሚሰጠዉን አገልግሎት እንዲረዱ ማድረግ አስችሏል ብሎ መዉሰድ ይቻላል፡፡

ከላይ የተጠቀሱትን እንደ ምሳሌ አነሳን እንጂ ሁሉም የሪፎርም ተግባራት በባለስልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍና ላይ ከፍ ያለ አስተዋጽዖ አበርክተዋል ብለን ማስቀመጥ እንችላለን፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዋናነት ባለስልጣኑ በትኩረት እያከናወናቸው የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን እንደ ሀገር ባለፉት ዓመታት ጀምሮ የተጀመረዉን የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ሪፎርም ሥራዎች በዝግጅት፣ በተግባር እና በማጽናት ምዕራፍ ከፋፍሎ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየፈፀመ ይገኛል፡፡ በሪፎርሙ ዝግጅት ምዕራፍ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት ለዜጎች ለማድረስ ተቋማዊ ተልዕኮዎችን ተወጥተናል ማለት ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህልም በሪፎርሙ 21 የሚጠጉ የአሠራር ሥርዓቶች በአዲስ መልክ ተዘጋጅተዉ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል፡፡

በሪፎርሙ የተግባር ምዕራፍ በዝግጅት ምዕራፍ የተዘረጉ የአሠራር ሥርዓቶችን ተጠቅሞ አገልግሎት መስጠትና አሠራሮችን በሙሉ ወደ ተግባር በመለወጥ የአገልግሎት አቅርቦት ጥራትንና ቅልጥፍናን ማሻሻል ሲሆን በሁለቱም ምዕራፎች ጠንካራ ተግባራት ተከናዉነዋል፡፡

በዋናነት በሁለቱ የሪፎርም ምዕራፎች የተከናወኑ ዓበይት ሥራዎች ስንመለከት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አደረጃጀትና አስተዳደር ሥርዓትን ለማሳለጥ የሚስችል ተቋማዊ አደረጃጀት በአዲስ መልክ ተሠርቷል፤ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ሠራተኞች የብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ሥርዓት መገንባትና የማስፈጸም አቅምን ማሳደግ የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቷል፤ ብዝኃነትንና አካታችነትን ያረጋገጠ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አስተዳደር ግንባታን የሚያፋጥንና ዘመናዊ የሠራተኞች አስተዳደር ስርዓት መገንባት የሚያስችል ተግባር ተከናዉኗል፤ ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ተደራሽ የአገልግሎት አቅርቦት ሥርዓት ተዘርግቶ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፤ ዲጂታል የአገልግሎት አሰጣጥ እና የተደራጀ ወቅታዊ መረጃ ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም የተቋሙን ተገባራት የሚረዳ (ገቢር ነበብ) የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አመራር እና ተቋም ግንባታን ማፋጠን የሚያስችሉ የአሠራር ሥርዓቶች ተተግብረዋል፡፡

እነዚህን ጠቅለል አድርገን አነሳን እንጂ በባለስልጣኑ በእያንዳንዱ ምሶሶ ስር በርካታ ተግባራት ተከናዉነዋል፡፡ በተለይም የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ህጎችን ከአዋጅ ቁጥር 1333/2016 አንፃር በመፈተሽ ከዓለም አቀፍ ስታንደርዶች ጋር ለማጣጣም በሚያስችል መልኩ ማዘጋጀትና ከአዋጁ ጋር የተናበበ የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017፣ የልማት ድርጅቶች የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1070/2017፣ የመድሀኒትና የህክምና መሳሪያዎች የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1066/2017 የመንግስት የንብረት አስተዳደር መመሪያ 1095/2017፣ የግንባታ ግዥ፣ የማዕቀፍ ግዥ፣ የምክር አገልግሎት ግዥ፣ ሌሎች አገልግሎቶች ግዥ እና የንብረት ሽያጭ የመደበኛ ጨረታ ሠነዶች (SBD) ተዘጋጅተዉ በሲስተም የማቀናጀት ሥራ ተሠርቷል፡፡

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአካል ጉዳተኞች የግዥና የንብረት የህግ ማዕቀፎችን (አዋጅ ቁጥር 1333/2016) በድምጽና በብሬን አዘጋጅቶ ተደራሽ የማድረግ ሥራም በሪፎርሙ የተከናወነ ተግባር ነዉ፡፡ ቀደም ሲል እንደተነሳው በሪፎርሙ ዝግጅት ምዕራፍ የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶች የተተገበሩ ሲሆን የተቋማዊ ለውጥ ሥራ አመራር ሥርዓት አተገባበር ማንዋል፤ የዕውቀት አስተዳደር (Knowledge Management) ማዕቀፍ መዘርጋት፤ ሠራተኞች የራሳቸውን ክፍተት በመፈተሽ አቅማቸውን ለማሻሻል የሚያገለግል የግለሰብ አቅም ማበልጸጊያ ዕቅድ (Personal Development Plan)፤ የውስጥ አሠራርና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡ የአሠራር ስርዓቶች ስርዓተ ፆታና ማህበራዊ ጉዳይ ማካተቻና መከታተያ ማኑዋል ተዘጋጅቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የተግባቦት፣ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽ ሥራዎች የሚመራበት ስትራቴጂ፤ የሠራተኞችን የአመራር አቅም ግንባታ ስትራቴጂ፤ በባለስልጣኑ የሚከናወኑ የግዥና ንብረት የኦዲት ሥራዎችን ክትትልና ቁጥጥር ማሳለጥ የሚያስችል የግዥና ንብረት ክዋኔ ኦዲት ማኑዋል፤ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ የውስጥ አጠቃቀም መመሪያ፤ የሲስተም ደህንነትን የሚያስጠብቅ ፖሊሲና የአሠራር ማዕቀፍ ተግባራዊነት፤ የባለስጣኑን አመራርና ሠራተኞች በብዝኃነትንና በአካታችነት ላይ ያተኮረ የአስተሳሰብ ግንባታ ሥርዓት፤ለሠራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢን መፍጠር፤ ፈጣን መረጃ ሰጪዎችን (Quick Quins) (የደረት ባጅ፣ የጠረጴዛ፣ በር ላይ የሚለጠፍ መረጃ ሰጪ፣ አስተያየት መስጫ መዝገብና ሳጥን) በማዘጋጀት የተገልጋዩን አስተያየትና ጥቆማ በመቀበል ግልጽ፣ ፍትሐዊ እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል፡፡     

ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ እያከናወናቸው ከሚገኙ ዓበይት ተግባራት አንዱ አገልግሎት አሰጣጥን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ ማድረግ ነው። በዚህም በሪፎርም ሥራችን ዲጂታላይዜሽን በትኩረት እየተተገበረ ይገኛል። ዲጂታላይዜሽንን ከመተግበር አንጻር በሪፎርም ሥራው የሚከተሉት ዓበይት ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

ባለስልጣኑ የመንግስት የኤሌክትሮኒክ የግዥ ሥርዓት (e-GP System) በየወቅቱ በመፈተሽና በማሻሻል ውጤታማነቱን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን የተሳካ ማድረግ የሚያስችል የውል አስተዳደር ሞጁል እና የንብረት ሽያጭ ማከናወን የሚያስችል ስርዓትም ሲስተሙ እንዲሠራ (configure) የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ የግዥና የንብረት አቤቱታ ማጣራት እና ጥፋተኛነት ሪፖርት ሥራን በመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት (e-GP system) ለማከናወን የሚስችል የሲስተም ማሻሻያ ሥራ ማከናወን ተችሏል፡፡ የመንግስት ግዥና ንብረትን በተመለከተ ለሚቀርቡ ሙያዊ ጥያቄዎች በኤሌክትሮኒክ ምላሽ መስጠት የሚስችል አሠራር መዘርጋት ተችሏል፡፡ በተጨማሪም ባለስልጣኑ የተሽከርካሪ ነዳጅና ቅባት ለማስተዳደር የሚያገለግል የተሽከርካሪ ስምሪትና አስተዳደር ሥርዓትን (e-fleet management system) ተግባራዊ ማደረግ ችሏል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን የባለስልጣኑን ድረ-ገጽ (www.ppa.gov.et) በአዲስ መልክ ማሻሻልና በመረጃ እንዲበለጽግ ማድረግ ተችሏል፣ በየነ መረብን (e-learning) በመጠቀም የማስተማር አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት በውስጥ አቅም በማልማት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ባለስልጣኑ ቀልጣፋና ዉጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን (e-GP system) ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች የአሠራር ስርዓቶች ጋር ማስተሳሰር የቻለ ሲሆን በተለይም ከብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት (National ID)፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ ከንግድ ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር (IFMIS)፣ ከባንክ፣ ከኢንሹራንስ አገልግሎት እና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ትስስር (Integration) የማድረግ ሥራ ተከናውኗል፡፡