Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

News

ባለስልጣኑ በአስተዳደራዊ ቅጣት ረቂቅ መመሪያ ላይ ከፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ጋር ውይይት አካሄደ፡፡

(መጋቢት 23/218)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግሥት ግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር ኃላፊነትን በአግባቡ ባለመወጣት የሚወሰዱ አስተዳደራዊ ቅጣቶች አፈፃፀም  ረቂቅ መመሪያ ላይ ከፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ ከግዥና ንብረት ሀላፊዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ መመሪያው የተጠያቂነት መላላትን ለማስቀረት፣ ጠንካራ የህግና የአሰራር ስርዓትን ለመፍጠር፣ ብልሹ አሰራርን እንዲወገድ ለማድረግ እንዲያስችል ተደረጎ መዘጋጀቱን ተናግረው፤ በረቂቅ መመሪያው ላይ ግልፅ ውይይትና ግንዛቤ መፍጠር በማስፈለጉ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

የውይይት መነሻ ጽሁፉን ያቀረቡት በገንዘብ ሚኒስቴር የህግ መመሪያ ሀላፊ አቶ ተወዳጅ መሀመድ በበኩላቸው ይህ መመሪያ እንዲወጣ አስቀድሞ በአዋጅ 1333/2016 የተቀመጠ ሲሆን መመሪያው በየደረጃው ያሉ ከግዥና ንብረት ጋር የተገናኙ ሀላፊዎችንና ባለሙያዎችን ሀላፊነት እንዲወጡ ለማስቻል ብሎም የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አስተዳደር ስራው በሀላፊነት እንዲሰራ ለማስቻል የተዘጋጄ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ረቂቅ መመሪያው በማንኛውም የመንግስት መ/ቤት የተሾመ ወይም የተመደበ ሰው ከግዥ አፈፃፀም እና ንብረት አስተዳደር ጋር በተገናኘ ዓመታዊ የግዥ ዕቅድን፣ የግዥ አፈጻጸም ሪፖርቶችን፣ የንብረት አስተዳደር ሪፖርት በተገቢው የጥራት ደረጃና ግዜ ካላቀረበ እንዲሁም ጥቅም ላይ የማይውሉ እና አገልግሎታቸውን የጨረሱ ንብረቶችን በወቅቱ አለማስወገድ ወይም እንዲወገዱ አለማድረግ እና ሌሌችንም ዝርዝር ጥፋቶችን አካቷል፡፡

ረቂቅ መመሪያው የተዘረዘሩትን ጥፋቶችን ፈፅሞ የተገኘ የስራ ኃላፊና ተሿሚ እንደጥፋት ደረጃውና ድግግሞሹ የተለያዩ ማስጠንቀቂያና የገንዘብ መቀጫ እንደሚጣልበት ያብራራል፡፡

በውይይቱ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በክብርት ዋና ዳይሬክተሯ እና በሚመለከታቸው የባለስልጣኑ የስራ ሀላፊዎች ምላሽና መብራሪያ ተሰጥቶባቸው ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

ባለስልጣኑ የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸምን ገመገመ፡፡

(መጋቢት 22/2018 ዓ/ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አመራርና ሰራተኞች የ2018 በጀት ዓመት የ9 ወራት እቅድ አፈጻጸምን በጋራ ገምገመዋል፡፡

ባለስልጣኑ ከተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ ከመንግስት ግዥና ንብረት ዲጅታላይዜሽን፣ ከዘለቄታዊነት የግዥና /Sustainable Procurement/ ንብረት አስተዳደር ሥርዓት ማጎልበት፣ ከመንግስት ግዥና ንብረት አገልግሎት እና መረጃ ጥራትና ሽፋን ማሳደግ፣ ከመንግስት ግዥና ንብረት የፖሊሲ፣ ማማከር አገልግሎት እና የጥናትና የምርምር፣ ከመፈፀምና ማስፈፀም አቅም ግንባታ፣ ሙያዊ ድጋፍ፣ ክትትል የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና ከመስጠት፣ ከስትራቴጂያዊ የቴክኒክ ትብብር እና አጋርነትን ከማጠናከር፣ ከመንግስት ግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል ሥራዎችን ጥራትና ሽፋን ከማሳደግ እንዲሁም ከግዥ አፈፃፀም እና ንብረት ሽያጭ ላይ የሚቀርቡ የይግባኝና የጥፋተኝነት ውሳኔ አሰጣጥን ከማጠናከር አንጻር የተቋሙን አፈጻጸም በጥልቀት ገምግሞ የቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

ባለስልጣኑ የአሰራር ስርዓቱን ጥራትና ቅልጥፍና ለማሳደግ አዋጁን ጨምሮ መመሪያዎችንና ሌሎች የአሰራር ስርዓቶችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን ከዲጂታላይዜሽን አንጻርም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP)፣ የተሸከርካሪ ስምሪት፣ ነዳጅ አጠቃቀም ሥርዓት (Fleet Management System)፣ የበየነ መረብ ትምህርት (e- learning) እና ሌሎች ዲጂታል አገልግሎቶችን እየተገበረ እንደሚገኝ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ተቋሙ በትኩረት እየተገበራቸው ከሚገኙ አበይት ዲጂታል ተግባራት አንዱ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP) ወደ ክልሎች ማውረድ መሆኑንና ቀድመው የጀመሩትን አዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና ኦሮሚያ ክልልን ከመደገፍ በተጨማሪ ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ለሶማሌ ክልል፣ ለአማራ ክልል እና ለድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር ስርዓቱን ሊተገብሩ በሚችሉብት ሁኔታ ላይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና እና የቴክኒክ ድጋፍ መሰጠቱም ተብራርቷል፡፡

በሪፖርቱ ከተብራሩና ተቋሙ በትኩረት ከሚያከናውናቸው አበይት ተግባራት አንዱ የኦዲት ስራ ሲሆን በ9 ወራት በ56 ተቋማት ላይ የህጋዊነት ኦዲት (93.3%)፣ በ38 ተቋማት ላይ የክትትል ስራ (100%)፣ በ13 ተቋማት ላይ የጥቆማ ኦዲት (100%) እንደተከናወነ በሪፖርቱ ተካትቷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ይግባኝና ጥፋተኝነትን በሚመለከት በ9 ወራት ውስጥ 174 የጥፋተኝነት ሪፖርት መረጃ ተሟልቶላቸው ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የቀረቡ ሲሆን 167 (95.97%) ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል:: በሌላ በኩል ይግባኝን በሚመለከት በ9 ወራት ውስጥ መረጃ ተሟልቶላቸው ከቀረቡ 101 ይግባኝ ውስጥ 98 (97%) ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም የሪፎርም ስራዎችን አጠንክሮ ማስቀጠል፣ የድጋፍና ስልጠና ስራዎችን ማጠናከር፣ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን ወደ ክልሎች ለማውረድ ተጨማሪ ስራ መስራት እንደሚያስፈልግ በዋና ዳይሬክተሯ ክብርት ወ/ሮ መሰረት አቅጣጫ ተቀምጦ ግምገማው ተጠናቋል፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ።

(መጋቢት 22/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ባለስልጣኑ የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍናን ለማሳደግና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያገኝ ለማስቻል እየተገበራቸው ከሚገኙ የዲጂታል ስራዎች አንዱ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP system) ስርዓት ነው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይህን ስርዓት በሁሉም የፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች እንዲተገበር ያስቻለ ሲሆን በመንግስት የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችም ስርዓቱን እንዲተገብሩት ለማስቻል የህግ ማዕቀፎችና የአሰራር ስርዓቶች ሲሰሩ ቆይተው ዛሬ ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆሊዲንግ ዋና ስራ አስፈጻሚ ክቡር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እና የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ናቸው።

በፊርማ ስነ- ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ክቡር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት የዲጂታል ኢትዮጵያን ጉዞ ለማፋጠን፣ ግልጽ፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ የግዥ ስርዓት ለማስፈን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP system) ስርዓት ከፍተኛ አስተዋፆ ያለው በመሆኑ በትኩረት እንሰራበታለን ብለዋል።

በሌላ በኩል የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በተለይም ባለስልጣኑ የግዥ ሂድቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

አክለውም የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ ተደራሽነትን በማስፋት፣ አሳታፊነትን በመጨመር፣ ወጪን በመቀነስ እና ግልጸኝነትን በማስፈን ረገድ ያለው ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ በትኩረት እየተሰራበት እንደሚገኝ አመላክተዋል።

አዲስ የተሾሙት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

 (መጋቢት 21/2018 ዓ.ም) የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አምራሮች አዲስ ለተሾሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሚኒልክ ሳሙኤል ደማቅ የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት አከናውነዋል፡፡

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት አዲስ የተሾሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሚኒልክ ሳሙኤል ወደ ባለስልጣኑ መቀላቀላቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸው በመሥሪያ ቤቱ በሚኖራቸው ቆይታ ስኬታማ የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም ክቡር አቶ ሚኒልክ ሳሙኤል ወደ ባለስልጣኑ መቀላቀላቸው ትልቅ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርና ለተቋሙ ርዕይ ስኬትም ጉልህ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡

ክቡር አቶ ሚኒልክ ሳሙኤል በበኩላቸው ወደ ባለስልጣኑ መቀላቀላቸ እንዳስደሰታቸው ገልጸው ለባለስልጣኑ ርዕይ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል፡፡