Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

General

ባለስልጣኑ የግዥ ባለሙያዎች በሚሰጥበት ስልጠና ላይ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አመራር ጋር ውይይት አደረገ።

(ታህሳስ 23/2018 ዓ.ም)፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የተቋማት ግዥ ባለሙያዎችን አቅም አጎልብቶ የግዥና ንብረት ጥራትና ቅልጥፍናን ለመጨመር እና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የግዥና ንብረት ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት አጫጭር ስልጠናዎችን እና ድጋፎችን እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዪኒቨስሪቲ ጋር አብሮ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት በፈጸመው መሰረት በቅርብ በሚጀምሩት የስልጠና ይዘቶች፣ አሰልጣኞች፣ የስልጠና ሁኔታ እና ስለ ሰልጣኝ የግዥና ንብረት ባለሙያዎች ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል።

በውይይቱ ማስጀመሪያ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ደረጄ እንግዳ (ዶ/ር) እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከግዥና ንብረት ባለስልጣን ጋር አብሮ በመስራቱ ደስተኛ እንደሆነና ውጤታማ ስራዎችን እንደምንሰራ አምናለሁ ብለዋል።

በሌላ በኩል የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤት በአዋጀ ከተሰጡት ተግባራት አንዱ ለግዥና ንብረት ባለሙያዎች የፕሮፌሽናላይዜሽን ስልጠና መስጠት በመሆኑ ይህን ስልጠና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማስኬድ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተመራጭ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል።

በእለቱ መሰረታዊ የሙያዊ ስልጠና (Basic Level Professionalism Training) እና የሥርዓተ-ትምህርት ይዘት እና የብቃት ማዕቀፍ (curriculum syllables and competency framework) ሰነዶች ለዩኒቨርሲቲው አመራር ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

ከገለጻው በኋላ ከዪኒቨርሲቲ አመራሮች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በባለስልጣኑ አመራርና ባለሙያዎች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
በእለቱ ከግዥናን ንብረት ባለስልጣን ባለሙያዎች ገለጻ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቭርሲቲ አበርክቶት ለውይይት ቀርቧል። የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡ ዶ/ር አከሊሉ ሲሆኑ ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ በተጨማሪ በጥናትና ምርምር፣ በማማከርና በካሪኩለም ቀረጻ ከፍተኛ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ያብራሩ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው በሙሉ አቅሙ ለማገዝ ፈቃደኛ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመጨረሻም አዲስ አበባ ሳይንስና ቲክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ጥናቶችን በመስራት፣ በማማከርና በማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች አቅም ያለው ተቋም በመሆኑ ውጤታማ ስራዎችን እንደምንሰራ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ለዚህም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ያሳየውን የማገዝና አብሮ የመስራት ፍላጎት አደንቃለሁ ሲሉ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የባለስልጣኑ አመራርና ሰራተኞች የተከሏቸውን ችግኞች ተንከባከቡ።

(ታህሳስ 22/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አመራርና ሰራተኞች “በመትከል ማንሰራራት” የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ሀምሌ 16/2017 ዓ.ም የተከላቸውን ችግኞች የመንከባከብና ውሀ የማጠጣት አከናውነዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በእንጥጦ ፓርኩ፣ በሸገር ከተማ አስተዳደር ኩራ ጅራ ክፍለ ከተማ፣ በምስራቅ ጉራጊዋ ቡኢ ከተማ እና በሌሎችም አካባቢዎች ከ30000 በላይ ችግኞችን የተከለ ሲሆን በእንጦጦ ፓርክ የተተከሉ ችግኞችን ዛሬ የመንከባከብና የውሃ የማጠጣት ስራ ሰርቷል።

በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ሰራተኞችን ያበረታቱት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት እንደገለጹት ችግኞችን መትከል ስኬታችን አይደለም። ይልቁንም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ስኬት ችግኞቹን ከመትከል በዘለለ ተንከባክቦ ለሚፈለጉት አገልግሎት እዲውሉ ማስቻል መሆኑንና ለዚህም የባለስልጣኑ አመራርና ሰራተኞች የተከሏቸውን ችግኞች መንከባከብ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።

ውሃ የማጠጣትና የመንከባከብ መርሃ ግብሩ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።

ድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር በቅርብ ቀን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP) ተግባር ላይ እንደሚያውል ተገለጸ።

(ታህሳስ 22/2018 ዓ.ም)፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP) መተግበር በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር ጋር ውይይት አድርጓል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አስቀድሞ ለከተማ መስተዳደሩ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ አፈጻጸም እንዲሁም ከአዋጅና ከመመሪያዎች ጋር ተያይዞ ስለሚፈጠሩ ለውጦች ተከታታይ ስልጠናዎች ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር የግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅና መምሪያ ከልሶ ወደ ስራ ለመግባት ከባለስልጣኑ ጋር ውይይት አድርጓል።

በእለቱ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይ እያደረገ ነው ብለዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በተለይም ባለስልጣኑ የግዥ ሂድቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን ያብራሩ ሲሆን በተለይም የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ ተደራሽነትን በማስፋት፣ አሳታፊነትን በመጨመር፣ ወጪን በመቀነስ እና ግልጸኝነትን በማስፈን ረገድ ያለው ሚና ከፍ ያለ መሆኑን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ አተገባበርን፣ ዓላማ፣ ተጠቃሚ እና አጠቃላይ ይዘትና ሂደትን በሚመለከት በኢጂፒ ፕሮጀክት የቴክኖሎጂ ዘርፍ ም/ማናጀር አቶ ያፌት መኮንን ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመጨረሻም ስርዓቱን በውጤታማነት ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከመጡ ባለሙያዎች ቀርቦ ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠባቸው ሲሆን ከተማ መስተዳደሩ በአጭር ጊዜ የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ  ግዥ ስርዓትን እንደሚተገብርም አንስተዋል። በሌላ በኩል ለትግበራው ባለስልጣኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ገልጸዋል።