ባለስልጣኑ የ2019 የአዲስ ዓመት ዋዜማን እና የ2018 በጀት ዓመት ስኬቶችን የሚገልጽ ልዩ የአብሮነት መርሃ-ግብር አካሄደ።

(ጳጉሜን 04/2018 ዓ.ም|አዲስ አበባ) – የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የሰራተኞችን ተነሳሽነት ለማሳደግ፣ አብሮነትን ለማጠናከር እና የ2019 የአዲስ ዓመት ዋዜማ ለማከበር ያለመ ልዩ የአብሮነት መርሃ-ግብር አካሄደ።
በመርሃ-ግብሩ ላይ በ2018 በጀት ዓመት የተከናወኑ አበይት ሁነቶችን እንዲሁም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ሂደት፣ አፈጻጸምና ስኬቶችን የሚያሳዩ አጫጭር ቪዲዮዎች ለታዳሚው ቀርበዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም በሰራተኞች መካከል መቀራረብን የሚያጠናክሩ የጠቅላላ እውቀትና ተቋማዊ ጥያቄና መልስ ውድድር የተካሄደ ሲሆን የ2019 ዓ.ም እቅድና የቃል መግባት መርሃ-ግብርም ተከናወኗል።
በመድረኩ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ለአዲሱ የ2019 ዓ.ም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ዋና ዳይሬክተሯ በንግግራቸው ባለስልጣኑ በ2018 በጀት ዓመት በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ጠቁመው ለተመዘገቡት ስኬቶች መላው የባለስልጣኑን ማህበረሰብ አመስግነዋል። ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም “አዲሱ ዓመት አብሮነታችንን እና ትጋታችንን የበለጠ አጠናክረን የባለስልጣኑን ራዕይ እውን የምናደርግበት እንዲሆን እየተመኘሁ፣ በግል ህይወታችሁም ስኬታማ እንድትሆኑ ከልብ እመኛለሁ” ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ ከባለስልጣኑ አመራርና ሰራተኞች በተጨማሪ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ላይ ልምድ ልውውጥ ላይ የሚገኙት የናይጀሪያ የመንግስት ግዥ ባለስልጣን ልዑካን ቡድን አባላትም ተገኝተዋል።
የልዑካን ቡድኑ ተወካይ በድረኩ ባደረጉት ንግግር ባለስልጣኑ ላደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል እና ላካፈላቸው ልምድ ከልብ የመነጨ ምስጋና አቅርበው “በተለይም በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት ዋዜማ በዚህ መልኩ ከባለስልጣኑ አመራርና ሰራተኞች ጋር ማክበር በመቻላችን እጅግ ደስተኞች ነን” ሲሉ ገልጸዋል።







0 Comments