Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የሴት ሰራተኞች ፎረም ዓመታዊ ጉባኤውን አካሄደ::

(ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም| አዲስ አበባ) — የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የሴት ሰራተኞች ፎረም የ2018 በጀት ዓመት ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 ዓ.ም. የሥራ አቅጣጫ ማስቀመጫ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በድምቀት አካሂዷል።

 

በመድረኩ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ባደረጉት ንግግር የሴት ሰራተኞች ተሳትፎ በዘመናዊ ተቋም ውስጥ ተጨማሪ ጉዳይ ሳይሆን የተቋሙ የልማትና የስኬት ዋና አካል መሆኑን ገልጸዋል። አክለውም ሴቶች በሙያቸው ብቻ ሳይሆን በአመራርነት፣ በውሳኔ አሰጣጥ፣ በፈጠራና በተቋማዊ ለውጥ አስተዳደር ላይ በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

 

ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም በተለይም ተቋማዊ የለውጥ ሥራዎች፣ የዲጂታል ሥርዓት ዝርጋታዎችና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ በሚከናወኑበት ወቅት የሴቶች ሙሉ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን በመጠቆም የሴት ሰራተኞችን የሙያና የአመራር አቅም ለማሳደግ ተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ሙሉ ቁርጠኝነት ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል።

ፎረሙ በ2019 በጀት ዓመትም የሴት ሰራተኞችን የሙያና የአመራር አቅም ማሳደግ፣ በውሳኔ አሰጣጥና በአመራር ደረጃ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማጎልበት እና  ፍትሃዊ የሥራ አካባቢንና የሥልጠና/ኮቺንግ እድሎችን ማጠናከር ላይ በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅበት ተቁመዋል።  

በመድረኩ ላይ የፎረሙ የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በወ/ሮ ሰናይት አንበሴ ቀርቦ በተገኙት ውጤቶች፣ በተለዩ ተግዳሮቶችና በቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች እና በ2019 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

 ከፎረሙ ዓመታዊ ውይይት ጎን ለጎን በባለስልጣኑ የቀን ማቆያ ቆይታቸውን አጠናቅቀው ወደ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ለሚገቡ ሕፃናት የሽኝት መርሃ-ግብር የተካሄደ ሲሆን ለሕፃናቱ የመማሪያ ቁሳቁስ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል። ይህ ድጋፍ ሰራተኞች የቤተሰብና የሥራ ኃላፊነታቸውን አጣጥመው እንዲወጡ ከተደረጉ ተቋማዊ ድጋፎች መካከል አንዱ ማሳያ መሆኑ ተመልክቷል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *