የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የቅደመ መደበኛ ትምህርትቤት ግንባታን በይፋ አስጀመረ።

(ነሐሴ 06 ቀን 2018 ዓ.ም) አዲስ አበባ — የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በክረምቱ ወራት ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጎን ለጎን አረጋውያንንና አቅመ ደካሞችን ከመመገብና የቁሳቁስ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቅድመ መደበኛ የትምህርት ቤት ግንባታን በይፋ አስጀምሯል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ሰዳል ወረዳ በሚገኘው ዲዛ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ሰባት ክፍሎች ያሉት አዲስ የትምህርት ቤት ግንባታ ያስጀመረ ሲሆን በእለቱ ለ100 ተማሪዎች የተመሪ ቦርሳን ጨምሮ ሙሉ የትምህርት ቁሳቁስ እርዳታ አበርክቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ፣ የሰዳል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፈረንጂ አባኬሻ፣ የባለስልጣኑ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች የክልልና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት በእለቱ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት መንግስት አቅመ ደካሞችን ከማገዝ ባሻገር የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በፅኑ መሰረት ላይ የመገንባት ስራ እየሰራ እንደሚገኝና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ሰው ተኮር ተልዕኮን አንገብጋቢ አድርጎ በመያዙ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በተለያዩ ጊዜያት ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሲወጣ መቆየቱን ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም “እዚህ የተገኘነው ህብረተሰቡን ለማየትና ለማዳመጥ፣ ተማሪዎችን ለማገዝ፣ ለነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማደጊያ የሚሆን ትምህርት ቤት ለመገንባት እና ከማሀበረሰባችን ጋር በመሆን ችግኝ ለመትከል ነው” ብለዋል። የትምህርት ቤቱ ግንባታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለተማሪዎች አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር የክልሉ እና የወረዳው አመራሮች ቅርብ ክትትል እንዲያደርጉ አደራ ያሉት ክብርት ወ/ሮ መሰረት ማህበረሰቡ ሕፃናትን የመንከባከብ፣ ሴቶችን የመደገፍ፣ ወጣቶችን የማሰራት እና ውቧን አካባቢ የበለጠ የማስዋብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አብዱላሂ በበኩላቸው በክረምቱ ወራት መንግስት የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን በማከናወን ወደ ህዝቡ ይበልጥ እየቀረበ እንደሚገኝ ገልፀው፣ ክልሉም በመሰል በጎ አድራጎቶች ላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። አክለውም ክልሉ እየተነቃቃ የመጣውን ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።







0 Comments