ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ መስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ።

(ነሐሴ 25/2018 ዓ.ም) — የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትንና ቅልጥፍናን ለማሳደግ እንዲሁም የዲጂታል አሰራርን ተደራሽነት ለማስፋት የሚያስችለውን ታሪካዊ የሁለትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተፈራረመ።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናን ለማረጋገጥ፣ አሰራሮችን ለማዘመን እና የመንግስት ሀብትና ገንዘብ የሚገባውን ተገቢ ዋጋ (Value for Money) እንዲያስገኝ ለማስቻል ዘርፈ-ብዙ ስራዎችን በከፍተኛ ቁርጠኝነትና ተነሳሽነት በማከናውን ላይ ይገኛል። ከእነዚህም ዋና ዋና ስራዎች መካከል የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን (e-GP system) በስፋት መተግበር አንዱ ሲሆን ባለስልጣኑ ስርዓቱን በሁሉም የፌዴራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ እንዲውል አድርጓል። በአሁኑ ወቅትም ይህንን ዘመናዊ አሰራር ቀድመው የጀመሩትን አዲዝ አበባ ከተማ መስተዳደርና እና ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ወደ ሌሎች ክልሎ ለማውረድ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።
የመግባቢያ ሰነዱን የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሚዴቅሳ ቶሎሳ በጋራ ተፈራርመውታል።
በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ወቅት ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት ባለስልጣኑ የአሰራር ስርዓቱን በማዘመን የህዝብና የተገልጋዮችን እርካታ ለማረጋገጥ በተነሳሽነት እየሰራ ይገኛል። ባለስልጣኑ የተጣለበትን ሀገራዊ ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትና የጀመራቸውን የዲጂታላይዜሽን ስራዎች ግብ ለማድረስ ከስልታዊ አጋር ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
አክለውም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሀገሪቱ ሰፊ የደንበኞች ቁጥርና አጠቃላይ ተደራሽነት ያለው ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም በመሆኑ ከባንኩ ጋር አብሮ መስራት የባለስልጣኑን ተገልጋዮች ከተንዛዛ እንግልት ለመታደግና ባሉበት ቦታ ሆነው ፈጣንና አስተማማኝ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሚዴቅሳ ቶሎሳ በበኩላቸው ባንኩ ሰፊ የቴክኖሎጂ ሽፋንና ዘመናዊ የዲጂታል ባንኪንግ መሰረተ-ልማት ያለው መሆኑን አብራርተዋል። በተጨማሪም ባንኩ ከበርካታ የመንግስትና የካምፓኒ ተቋማት ጋር በጥምረትና በቅንጅት የመስራት የካበተ ልምድ እንዳለው ያወሱት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ከመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ጋር ተቀናጅቶ መስራት ለባንኩ ተጨማሪ እሴት የሚፈጥርለት መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ የባንኩን የዲጂታል ክፍያና የፋይናንስ አገልግሎት ከኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ ስርዓት (e-GP) ጋር በማስተሳሰር የግዥ ሂደቱን የበለጠ ግልጽ፣ ፈጣን እና ተደራሽ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።




0 Comments