ባለስልጣኑ በተቋማዊ ባህል፣ በዘላቂ የመንግስት ግዥና በንብረት አወጋገድ ዙሪያ ከሰራተኞች ጋር ተወያየ።

(ነሐሴ 23/2018 ዓ.ም |አዲስ አበባ) — የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የተቋሙን አሰራር ለማጠናከር፣ የአካባቢ ጥበቃን ያገናዘበ አሰራርን ለመዘርጋት እና የስራ ቦታ ፕሮቶኮልን ለማሻሻል የሚያስችሉ ሶስት ዋና ዋና ሰነዶችን መሰረት በማድረግ ከሰራተኞቹ ጋር የውይይት መድረክ አካሄዷል።
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት ተቋሙ የተጣለበትን ሀገራዊ ሀላፊነት በብቃት ለመወጣት ጠንካራ ተቋማዊ ባህል መገንባትና ዘመናዊ የአሰራር ስልቶችን መከተል ወሳኝ መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን የሚዘጋጁ አሰራሮችና ማኑዋሎች ወደ ተግባር የሚቀየሩት በሰራተኛው ሙሉ ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት በመሆኑ መሰል የውይይት መድረኮች ያላቸውን ከፍተኛ ሚና አጉልተው አሳይተዋል።
ተቋማዊ ባህል፣ አለባበስና ፕሮቶኮል የውስጥ መመሪያ ላይ ገለጻ ያቀረቡት በባለስልጣኑ የኢጂፒ ፕሮጀክት ማናጀር አቶ ያፌት መኮንን ሲሆኑ መመሪያው የተቋሙን በጎ ገጽታ የሚገነቡ የሙያ ስነ-ምግባር መርሆች፣ የስራ ቦታ አለባበስ ስታንዳርዶች እና የፕሮቶኮል ስርዓቶችን በጥንቃቄ መተግበር እንደሚገባ አመላክተዋል።
በሌላ በኩል ዘላቂነት ያለው የመንግስት ግዥን በሚመለከት የባለስልጣኑን የሦስት አመት እቅድ ያቀረቡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የማሻሻያ እና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ በአቶ መላኩ ተጓዴ የቀረበ ሲሆን የመንግስት ግዥ አሰራር ከኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባሻገር የአካባቢ ጥበቃንና የማህበራዊ ሀላፊነትን ያገናዘበ (Green Public Procurement) እንዲሆን የሚያስችሉ ስልታዊ አቅጣጫዎችን መከተል እንዳለበት አመላክተዋል።
አቶ መላኩ ከዘላቂ የመንግስት ግዥ እቅድ በተጨማሪ በጤናና በአካባቢ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ከአገልግሎት ውጪ የሆኑ ንብረቶች አያያዝ፣ አጠባበቅ እና አወጋገድ ማኑዋል ላይ ገለጻ አቅርበዋል። አቶ መላኩ በገለጻቸው ከአገልግሎት ውጪ የሆኑና ለጤናም ሆነ ለአካባቢ ስጋት የሚደቅኑ ሀብቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመያዝ፣ ለመጠበቅና ለማስወገድ ባለስልጣኑ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ጥናት እንዳስጠና እና ጥናቱን ተከትሎም የአፈጻጸም ማኑዋል እንዳዘጋጄ ገልጸው እነዚህን ንብረቶች በሰው ጤናም በአካባቢ ላይ ጉዳት ሳያደርሱ ማስወገድ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
ከሰነዶቹ መቅረብ በኋላ ከተሳታፊ ሰራተኞች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።





0 Comments