Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በክልሎች በውጤታማነት እንዲተገበር የተቀናጀ ድጋፍ እና ክትትል አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ።

(ነሐሴ 14/2018 .)– የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የባለስልጣኑን የመንግስት የአገልግሎትና አስተዳደር የሪፎርም አፈጻጸምን በሚመለከት ለክክልል ፋይናንስ እና ግዥ ሀላፊዎች ልምድ የማከፈልና የውይይት መድረክ አካሂዷል።

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በንግግራቸው የሪፎርም ስራው ዋና አላማ ግልጽነትን፣ ብቃትና ውጤታማነትን ያረጋገጠ አካታች የሲቪል ሰርቪስ ስርዓት መገንባት መሆኑን አመላክትዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት አክለውም ባለስልጣኑ የሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍን በውጤታማነት አጠናቆ ወደ ትግበራ ምዕራፍ እንደተሸጋገረ እና በአሁኑ ወቅት ወደ ማጽናት ምዕራፍ ለመሸጋገር በትጋት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በንግግራቸው ባለስልጣኑ ሁሉንም የአገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታል የማድረግ ስራ ማከናወኑንና አብዛኞቹ የአሰራር ስርዓቶች በውስጥ አቅም የተሰሩ በመሆናቸው የመንግስትን ሀብት የመቆጠብና የሰራተኞችን አቅም የማበልጸግ እድል መፍጠራቸውን ጠቁመዋል። ሪፎርሙ ውጤታማ የሚሆነው በአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን ሁሉን አቀፍ እና አካታች ሆኖ ሲተገበር በመሆኑ የክልል አመራሮችም የላቀ ቁርጠኝነት በማሳየት ልምድ እና ምርጥ ተሞክሮዎችን ማስፋት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

በመድረኩ የባለስልጣኑ የአገልግሎትና አስተዳደር የሪፎርም አፈጻጸም ሪፖርት በመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያ እና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ተጓዴ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በሌላ በኩል በፌዴራል ደረጃ እየተተገበረ የሚገኘው የሪፎርም ስራ ውጤታማነት በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች ሳይደበዝዝ በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲተገበር በባለስልጣኑ የሚሰጠውን ሙያዊ ድጋፍ፣ የስልጠና እና የክትትል ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ከተሳታፊዎች ተነስቷል።

በመጨረሻም ክልሎች አዳዲስ ህጎችን ማውጣት ሳይጠበቅባቸው ባለስልጣኑ ያዘጋጃቸውን አሰራሮች ከነባራዊ ሁኔታቸው ጋር አጣጥሞ መጠቀም የሚችሉ መሆናቸውንና ባለስልጣኑ የስልጠና፣ የምክር እና ተያያዥ ድጋፎችን እንደቀድሞው ሁሉ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የባለስልጥኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት አረጋግጠዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *