Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

በአማራ ክልል የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን (e-GP) ተግባራዊ ለማድረግ የዝግጅት ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

(ነሀሴ 05/2018 ዓ.ም)፣ ባህር ዳር — በኢፌዴሪ የመንግሥት ግዥ እና ንብረት ባለሥልጣን እና በአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ትብብር የሚሰጠው የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት (e-GP) የሥልጠና ፕሮግራም በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል። ሥልጠናው በ2019 ዓ.ም አዲሱን አሠራር በክልሉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ታስቦ ለተመረጡ አስር የክልሉ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች እና የግዥ ባለሙያዎች እየተሰጠ የሚገኝ ነው።

የአማራ ክልል ገንዘብ ቢሮ ኀላፊ አቶ አታላይ ጥላሁን በስልጠናው ወቅት እንደገለጹት የመንግስት አሠራርን በዲጂታል ቴክኖሎጂ የማዘመንና አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ የማድረግ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ ይገኛሉ። የሕዝብ ሃብትን በቁጠባ እና በተቀላጠፈ መልኩ ለማስተዳደር የሚያስችለውን አዲሱን የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት በ2019 ዓ.ም በክልሉ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ፣ የመመሪያ እና የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ዝግጅቶች እየተደረጉ እንደሆነም አብራርተዋል። አክለውም የአስሩ ተቋማት የሙከራ ትግበራ ስኬታማነት በመገምገም ሥርዓቱን እስከ ታችኛው የመንግሥት እርከን ለማስፋት ትልቅ መሠረት መሆን እንዳለብት አመላክተዋል።

በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ፕሮጀክት የአቅም ግንባታ አስተባባሪ አቶ ደበበ ማሞ እንደገለጹት በበኩላቸው ባለስልጣኑ የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራት፣ ግልጽነት እና ቅልጥፍናን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ የአሠራር ሥርዓቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል የማድረግ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ያብራሩ ሲሆን የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት በ2014 ዓ.ም በዘጠኝ የፌዴራል ተቋማት በሙከራ ደረጃ ተጀምሮ በአሁኑ ወቅት በሁሉም የፌዴራል ተቋማት፣ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ በሙሉ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተተገበረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

አቶ ደበበ አክለውም አሠራሩ ከወረቀት እና ከሰው ንኪኪ ነፃ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና አስተማማኝ በመሆኑ ወጥ የሆነ ሀገራዊ አሠራር ለመዘርጋት ሥርዓቱን ወደ ክልሎች የማውረድ ሥራ በስፋት እየተሠራ መሆኑንና ተመሳሳይ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ለሌሎች ክልሎችም እየተሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በተጨማሪም አብዛኞቹ ክልሎች የየራሳቸውን የግዥ ሕግ ከፌዴራሉ የግዥ ሕግ ጋር የማጣጣም እና የማስማማት ሥራዎችን በስፋት እያከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

በሥልጠናው እየተሳተፉ የሚገኙ የግዥ ባለሙያዎች በበኩላቸው እስካሁን የነበረው ወረቀትን መሠረት ያደረገ አሠራር የተንዛዛ፣ ለአሠራር ግልጽነት አጠራጣሪ እና አሰልች እንደነበር ገልጸው የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱ መተግበሩ ጊዜን፣ ጉልበትን እና ወጭን ከመቆጠቡ ባሻገር ሙስናን በመከላከል እና እንግልትን በማስቀረት አገልግሎቱን በከፍተኛ ሁኔታ ያቀላጥፋል ብለዋል።

በመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ባለሙያዎች እና አስተባባሪዎች እየተሰጠ የሚገኘው ይህ አቅም የመገንባት ሥልጠና ለሚቀጥሉት ቀናት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ታውቋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *