የተዘረጋው የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቋሚ ኮሚቴ አመራር

(ጥር 02/2018 ዓ.ም)፣ የመንግስት ግዥን ንብረት ባለስልጣን ከኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢዎች፣ ከፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከአማካሪ ኮሚቴ አመራር እና ከምክር ቤቱ ሴቶች ኮከስ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ እንደገለጹት ግዥ ውስብስብና ከፍተኛ የመንግስት በጀት የሚፈስበት በመሆኑ ይህን ውስብስብና ከፍተኛ በጀት የሚፈስበትን ስራ ዲጂታላይዝ በማድረግ በማኑዋል ግዥ ሲታዩ የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍና የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ በማድረግ በኩል ባለስልጣኑ የሄደበት ርቀት እጅግ የሚያኮራና የሚያስመሰግን ነው። ስለሆነም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የበለጠ ስኬታማ እንዲሆን ቋሚ ኮሚቴው የበለጠ ማገዝ ያስፈልጋል ብለዋል።
ውይይቱ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን እያከናወናቸው በሚገኙ ክንውኖች፣ የዲጂታል ስራዎች፣ የግዥና ንብረት የህግ ማዕቀፎች እና ወደፊት በትኩረት ሊሰራባቸው በታቀዱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በገለጻቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ፣ ጥራቱን የጠበቀ፣ ከአድልዖ የጸዳና አሳታፊ ለማድረግ ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ የማድረግና ከእጅ ንክኪ ነጻ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል። በዚህ ረገድ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP System)፣ የተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ስርዓት (e-Fleet Management)፣ ዲጂታል ደብዳቤ መላኪያ፣ መቀበያ (e- lettering) እና ሌሎችም ስርዓቶችን የፌዴራል የመንግስት ተቋማት ጭምር እንዲተገብሩት በማድረግ ባለስልጣኑ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንዳለ ተብራርቷል።
በውይይቱ ባለስልጣኑ እጅግ ዘመናዊ የግዥና ንብረት አሰራር ስርዓት እንደዘረጋና ይህም ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል። የምክር ቤቱ አባላት እንደገለጹት ሀገር የጀመረችውን የእድገት ጎዳና እውን የምታደርገው ጠንካራ እና ውጤታማ ተቋማትን መፍጠር ሲቻል ነው። በዚህ በኩል የባለስልጣኑ ዲጂታል ስራዎች በዚህ ይስተካሉ የሚባሉ አይደሉም፤ በተለይም አገልግሎቱን ወደ መሶብ አንድ ማዕከል ማስገባቱ እና ክልሎችን ወርዶ መደገፍና ስርዓቱ እንዲሰፋ ለማድረግ የተደረገው ጥረት እጅግ የሚመሰገን ነው። ስለሆነም ስራዎችን ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
በመጨረሻም ከምክር ቤቱ አመራርና አባላት የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን በዋና ዳይሬክተሯ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው ውይይቱ ተጠናቋል።
ለበለጠ መረጃ፤
ድረ ገጽ፡ www.ppa.gov.et
ፌስቡክ፡ Public Procurement and Property Authority
ቴሌግራም: Public Procurement and Property Authority/የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን











0 Comments