የሀረሪ ክልል የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዢ ስርዓትን ለመተግበር በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ ርዕሰ መስተዳደሩ ገለጹ፡፡

(ሚያዝያ 25/2018 ዓ/ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥና ንብረት ስርዓቱን አዘምኖ የመንግስት ገንዘብ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኝ ለማስቻል ከሚተገብራቸው ዲጂታል ተገባራት አንዱ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት (e-GP System) ሲሆን ስርዓቱን በሁሉም የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ከማስተግበር ባሻገር ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች እንዲተገብሩት ለማስቻል ውይይት እያደረገ፣ ስልጠና እየሰጠና የክልልና የከተማ መስተዳደሮች የግዥና ንብረት ህጎች ከፌዴራሉ የግዥና ንብረት ህጎች ጋር እንዲጣጣሙ እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡
በዚህም ባለስልጣኑ በዛሬ እለት ከሀረሪ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስርዓቱን መተግበር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የፌደራል የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ሲሆኑ ኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ያደረገ በመሆኑ ተወዳዳሪን የሚጨምር፣ አሳታፊ፣ ከገጽ ለገጽ ግንኙነት የጸዳ በመሆኑ ብልሹ አሰራሮችን የሚቀንስ፣ ወጪ ቆጣቢ ብሎም የህግ መከበርን የሚያረጋግጥ ስርዓት ነው ብለዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት አክለውም ስርዓቱ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ዋጋ በማስገኘትም ሀገሪቱ የያዘችውን ዲጂታል ኢኮኖሚ የሚያግዝ ስርዓት በመሆኑ ሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች ሊተገብሩት ይገባል ያሉ ሲሆን በትግበራ ሂደት ለሚፈጠር ችግር ድጋፍ እንዲሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ የግዢ ሥርዓት ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመቅረፍና ቀልጣፋ የግዢ ስርዓት በማስፈን ረገድ ጉልህ ፋይዳ አለው ያሉ ሲሆን ስርዓቱ በክልሉ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን ይሰራል ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የክልሉ የአስፈጻሚ፣ የሕግ አውጪ እና የተቆጣጣሪ ተቋማት አመራሮች ተሳትፈዋል።





0 Comments