ዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement)ምንድን ነው?
ዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement) ማለት የመንግስት ተቋማት ዕቃዎችን፣ አገልግሎቶችን እና የግንባታ ሥራዎችን በሚገዙበት ጊዜ የኢኮኖሚ ብቃትን፣ የአካባቢ ጥበቃን እና ማህበራዊ ኃላፊነትን ከግንዛቤ በማስገባት የሚፈጸም የግዥ ሂደት ነው።
ዘላቂነት ያለው ግዥ የሚያተኩረው በዋጋ ላይ ብቻ ሳይሆን በረጅም ጊዜ ጥቅም፣ በአካባቢ ላይ በሚያሳድረው ተፅዕኖ እና በማህበራዊ ጥቅሞች ላይም ጭምር ነው።
እንደሚታወቀው የመንግስት ተቋማት ከበጀታቸው ትልቁን ድርሻ የሚወስደው በግዥ ስራ ላይ የሚያወጡት የሚያውሉ ወጪ ነው፡፡ እነዚህም የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የጤና አገልግሎቶች፣ የትምህርት ቁሳቁሶች፣ ትራንስፖርት እና የህዝብ አስተዳደርን ያካትታሉ። ስለሆነም በተለምዷዊ የሚከናወነው ግዥ በዋናነት ምርቶችን በዝቅተኛ ዋጋ ማግኘት ላይ ያተኮረ ነበር። ይሁን እንጂ በዘመናዊ የግዥ ሥርዓት ከዋጋ በተጨማሪ ዘላቂነት ያለው የግዥ ስርዓትን መተግበር መሰረታዊ ጉዳይ ሆኗል።
ዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement) የሀገርን ኢኮኖሚ የሚያነቃቃ፣ ማህበራዊ ትስስርን የሚያጠናክር እና የአካባቢ ጥበቃን የሚያግዝ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ብዙ አገሮች እንደ ስትራቴጂካዊ መሳሪያ በመጠቀም የአካባቢ ጥበቃን ለማበረታታት፣ ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን ለመደገፍ፣ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር እና ሥነ-ምግባራዊ የንግድ ልምዶችን ለማበረታታት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። የዚህ ዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement) ዋና ዓላማ የመንግስት ወጪ ዘላቂ ልማትን እንዲደግፍ ማድረግ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜም ለተከፈለው ገንዘብ ተመጣጣኝ ዋጋ (Value for Money) እንዲገኝ ማረጋገጥ ነው፡፡
በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ውስጥ ዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement) ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለድህነት ቅነሳ እና ለአካባቢ ጥበቃ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።
ዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement) በዋናነት ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ እነዚህም የኢኮኖሚ ዘላቂነት፣ የአካባቢ ዘላቂነት እና የማህበራዊ ዘላቂነት ናቸው፡፡ ይህም ዘላቂ የመንግስት ግዥ ዝቅተኛ ዋጋ ያለውን ምርት ከመምረጥ በላይ ይሄዳል። በዚህ ሂደት የግዥ ባለሙያዎች የምርቶችን እና የአገልግሎቶችን አጠቃላይ የህይወት ዑደት ወጪ (life-cycle cost) እና ሰፊ ተፅዕኖዎቻቸውን በመገምገም በኩል ያላቸው ድርሻ የጎላ ነው።
በዘላቂ የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement) ስርዓት መሰረት ኃይል ቆጣቢ መሳሪያዎችን መግዛት በጊዜ ሂደት የኤሌክትሪክ ወጪን ይቀንሳል፣ ለአካባቢ ተስማሚ የሆኑ ምርቶችን መግዛት ብክለትን ለመቀነስ ይረዳል እንዲሁም ሀገር በቀል አቅራቢዎችን መደገፍ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የሀገርን ኢኮኖሚ ይደግፋል፡፡ ስለዚህ ዘላቂ ግዥ የፋይናንስ ብቃትን ከአካባቢ እና ከማህበራዊ ኃላፊነት ጋር በማመጣጠን የሚከናወን የግዥ ስርዓት ነው።

0 Comments