የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በመንግስት ቋሚ ንብረት አስተዳደር እና በስቶክ አስተዳደር ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ሥልጠና ለሚመለከታቸው የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከታህሳስ 6-10 ቀን 2007 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ሰጠ ፡፡
የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት የስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ደበበ ማሞ እና የጥናትና መረጃ ትንተና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ደምሱ አብዲ ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን የስልጠናው ዋና ዓላማ ውጤታማና የስቶክ አስተዳደር መርህንና ሥርዓትን እንዲረዱ፣የስቶክ አስተዳደር ተግባራትን የማከናወን አቅም ለማዳበር በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት የንብረት አስተዳደር እና የስቶክ አስተዳደር ህግጋትንና ሥርዓትን ጠንቅቀው እንዲያወቁ ግንዛቤ ለመስጠት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
አሰልጣኞቹ አጠቃላይ ስያሜን፣ስቶክ መለየትና መመደብን፣መቀበል እና መፈተሽን፣ወጪ ማድረግን ፣የስቶክ መዛግብት የሂሳብ ሪፖርትን፣ስቶክ ቆጠራና ቁጥጥርን፣ክምችትን፣ መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳቦችና መርሆዎችን፣በመንግስት ይዞታ ስር የሚገኙ ቋሚ ንብረቶች የአስተዳደር መዋቅር፣የመጀመሪያ አጠቃላይ ቆጠራ እንቅስቃሴና የመዝገብ ዝግጅት ሂደት ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡