Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

News

ባለስልጣኑ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ አካሄደ።

(ሰኔ 13 ቀን 2018 ዓ.ም)፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዝግጅትን በተመለከተ ከሠራተኞቹ ጋር ሰፊ የውይይትና የገምገማ መድረክ አካሂዷል።

የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸምና የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድን ያቀረቡት የባለስልጣኑ የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል ገረመው ሲሆኑ ባለፈው በጀት ዓመት ባለስልጣኑ ዘመናዊ፣ ግልጽና ተጠያቂነትን የተላበሰ የግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት በርካታ ተግባራትን እንዳከናወነ አብራርተዋል። አቶ ዳንኤል በሪፖርታቸው በተለይም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት (e-GP) አጠቃቀምን በውጤታማነት መመራት፣ የአቅም ግንባታ ስራን ማጠናከር፣ የህግ ማዕቀፎችን ተፈጻሚነት መከታተልና ማስፈጸም እንዲሁም የሀብት አጠቃቀምን ማሳደግ ላይ ከፍተኛ ስራ መሰራቱን አመላክተዋል። 

በዚህም በበጀት ዓመቱ በሲስተም ግዥ የሚፈጽሙ ተቋማት ቁጥር 367 መድረሱን፣ ለ13,913 ባለሙያዎችና አቅራቢዎች በተለያዩ ዘርፎች ሥልጠና መሰጠቱን፣ የአዋጅ ቁጥር 1333/2016 ማስፈጸሚያ መመሪያዎች ሥራ ላይ መዋላቸውን ተከትሎ 42 የሚደርሱ መደበኛ የጨረታ ሰነዶች እና ሌሎች የአሰራር ስርዓቶች መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።  

አቶ ዳንኤል አክለውም በ2018 በጀት ዓመት የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን መሠረተ ልማት ውስንነት፣ የክህሎት ልዩነትና የኢንተርኔት መቆራረጥ በዋናነት ተግዳሮት የነበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ እነዚህን ተግዳሮቶች በመፍታት የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓትን ሙሉ ትግበራ ማረጋገጥ፣ የመንግስት ንብረት ዲጂታል ምዝገባን ማሻሻልና የመረጃ ጥራትን ማጠናከር ላይ በትኩረት እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም ከሰራተኞች የተለያዩ ጥያቂዎች እና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በእለቱ የማጠቃላያ ንግግር ያደረጉትና የቀጣይ የስራ አቅጣጫ የሰጡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው ተቋሙ ዘመናዊ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓትን በማጠናከር በ2022 ዓ.ም በአፍሪካ አርአያ ከሆኑ ተቆጣጣሪ ተቋማት አንዱ ለመሆን የሰነቀውን ራዕይ ለማሳካት እያንዳንዱ የሥራ ክፍልና ባለሙያ በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስበዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በሰጡት የስራ አቅጣጫ በ2019 በጀት ዓመት የታቀዱትን የዲጂታል ለውጥ ስራዎችን ማፋጠን፣ የአቅም ግንባታ ስራዎችን ማጠናከር፣ የኢፍሊት ትግበራን ማሳደግ፣ የሥርዓት ትስስርን ማሻሻልና ጠንካራ የቁጥጥርና የኦዲት አቀራረብን መተግበር የመንግስትን ሀብት በአግባቡ ለመጠበቅና ብክነትን ለመቀነስ ወሳኝ መሆናቸውን በመግለጽ ሠራተኛው ለዕቅዱ መሳካት የበኩሉን እንዲወጣ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።

ባለስልጣኑ “ከምርጫ ማግስት: ጠንካራ መንግስት” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት አካሄደ።

(ሰኔ 12/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ፡ ከዜግነት ግዴታ እስከ ተቋማዊ እምርታ በሚል መሪ ሀሳብ ከሰራተኞች ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ሲሆኑ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት የሁሉም ሰራተኛ ሀላፊነት መሆኑን አመላክተው ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ሰራተኛው የህዝብን ፍላጎት የሚያሳካ፣ የመንግስትን ንብረት የሚጠበቅ፣ ፈጣንና ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጥ፣ ሀገራዊ ትልሞችን አውቆ የሚተገብር መሆን አንዳለበት ገልጸዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት መንግስት ሰላምና መረጋጋት የማረጋገጥ፣ ፖለቲካዊ ውጥረቶችን በውይይት የመፍታት፣ የተቋማትን አቅም የማጎልበት፣ የህዝብን ጥያቄ የመመለስ፣ ዲጂታል ስራዎችን በትኩረት የመተግበር፣ ተቋማትንና የሰራተኞችን አቅም ማጎልበት ላይ በትኩረት የሚሰራ ሲሆን እንደ ተቋም ተገቢውን የቁጥጥር ስራ በትኩረት መስራት፣ ኢፍሊት ማናጅመንትን ወደ ተሟላ ትግበራ ማስገባት፣ ተቋማትን መደገፍ፣ ዲጂታል ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና ቅልጥፍናን ማረጋገጥ፣ የተጀመረው የሪፎርም ስራ ዳር ማድረስ እና ሙስና እና ብልሹ አሰራርን መከላከል በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር ክቡር አቶ ሚኒሊክ ሳሙኤል በበኩላቸው ከምርጫ ማግስት መንግስትነትን የሚረከበው ፓርቲ አሸናፊነትን እንደ ድል ሳይሆን እንደ ድርብ ሀላፊነት ወስዶ ሀገር የጀመረችውን ሁለንተናዊ እድገት ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በተለይም ተቋማዊ አገልግሎትን ማጠናከር፣ የዜግነትና ተቋማዊ ሀላፊነትን ማሳደግ እንዲሁም ሀገረ መንግስትን ማጽናት ላይ በትኩረት ማስራት እንደሚያስፈልግ ያመላከቱ ሲሆን ሰራተኞች የተሰጣቸውን ሀላፊነት በአግባቡ በመወጣት ለሀገረ መንግስት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ መወጣት አለባቸው ብለዋል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተሰጥተው በተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ምላሽና ማብራሪያ ውይይቱ ተጠናቋል።

ባለስልጣኑ የስልጠና አሰጣጥን ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመ።

(ሰኔ 09/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥና ንብረት ፕሮፌሽናላይዜሽን ስልጠናን ከፍ ለማድረግ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል። የመግባቢያ ስምምነቱ የግዥና ንብረት አስተዳደር የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ፕሮግራምን በጋራ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ ሲሆን የግዥና ንብረት ባልሙያዎችን በስነ- ምግባር የታነጹ እንዲሁም ሁለንተናዊ አቅምን፣ ሙያዊ ብቃትን እና አፈፃፀምን ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።

በፊርማ ስነ- ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት ስምምነቱ በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን እና በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ መካከል የተመሰረተ የስትራቴጂክ ትብብር ምልክት ሲሆን በኢትዮጵያ የመንግሰት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ስርዓት ላይ ብቃት ያለው ባለሙያ ለማፍራት የተደረገ አስፈላጊ እርምጃ መሆኑን አመላክተዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም የትብብር ስምምነቱ ዋና ዓላማ ባለሙያዎችን ማብቃትና ማሻሻል፣ የግዥ ሕጎችን በትክክል ማስፈጸም የሚችሉ ባለሙያዎች ማፍራት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት እና ብቃት ያለው የሀብት አጠቃቀም ማሳደግ፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተደራጀ የስልጠና ስርዓት ማቋቋም መሆናቸውን አብራርተዋል።

ክብርት ዋና ዳይሬክተሯ የግንኙነትና የስራ ሰንሰለቱን ሲያብራሩ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ፕሮግራሙ ላይ የፖሊሲ አቅጣጫ መስጠት፣ የስልጠና ይዘት ማዘጋጀት፣ ሰልጣኞችን እና አሠልጣኞችን መምረጥ፣ የግምገማ ሂደት መምራት እና ሰርተፊኬት መስጠትን በሚመለከት በከፍተኛ ሀላፊነት የሚሰራ ሲሆን አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ እንደ ዋና የአካዳሚክ ተቋም የስልጠናውን ዕለታዊ አስተዳደር፣ የመማሪያ አካባቢ አቅርቦት፣ የሠልጣኝ ሁኔታ ክትትል እና በሁሉም ሂደቶች ባለስልጣኑን በማማከር  በኩል በከፍተኛ ትጋት ሀላፊነቱን እንደሚወጣ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ደረጄ (ዶ.ር) በበኩላቸው ስምምነቱን እውን የሚያደርጉ ስራዎች አስቀድሞ ሲሰሩ መቆየታቸውን አውስተው ስምምነቱ ሁለንተናዊ ብቃትን የተላበሰ የግዥና ንብረት ባለሙያ ለመፍጠር እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዘላቂ የመንግስት ግዥ አተገባበርን በብቃት ለመወጣት ምን እያከናወነ ነው?

እንደሚታወቀው የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአሰራር ስርዓቱን በማዘመን በአፍሪካ አርዓያ ከሆኑ የመንግስት ግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ ተቋም የመሆን ራዕይን ቀርጾ በትጋት የሚሰራ ተቋም ነው፡፡ በዚህም ሁሉንም የአገልግሎት አሰጣጥ ዲጂታል ማድረግ ችሏል፡፡ በተለይም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት ሀገራችን የያዘችውን ዲጂታል ኢኮኖሚ በመደገፍ በኩል ያለው ሚና ላቅ ያለ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ባለስልጣኑ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ የሪፎርም የትግበራ ምዕራፍን በብቃት እየተወጣ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ በዚህ የሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ ብዙ የአሰራር ስርዓቶች የተቀረጹ ሲሆን በትግበራ ምዕራፉ ደግሞ የአሰራር ስርዓቶችን ስራ ላይ አውሏል፡፡

ስለሆነም በዚህ  የዝግጅትና የትግበራ ምዕራፍ ከተከናወኑ ተግባራ አንዱ ቀጣይነት ያለው የመንግስት ግዥ (Sustainable Public Procurement manual) ማዘጋጀት ሲሆን ማኑዋሉ ተዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት የማድረግ ና ስልጠና የመስጠት ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በመሆኑም እንደ ሀገር ዘላቂ የግዥ አሠራሮች የኢንዱስትሪ ልማት የሚያረጋግጡ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን የሚያበረታቱ፣ በአካባቢ ላይ ጉዳት የማያደርሱ፣ ድህነትን ቅነሳ ላይ ትኩረት የሚያደርጉ፣ የሀገሪቱን አረንጓዴ ኢኮኖሚ ወይም ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲደግፉ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ዘላቂነት ያለው የመንግስት ግዥን (Sustainable Public Procurement) በሚመለከት በፌዴራል ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1333/2016 አንቀጽ 28 ንዑስ አንቀጽ አንድ  የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንደ ግዥው ባህርይ ከአካባቢ ብክለት የፀዳ፣ መልሶ መጠቀምን፣ የህይወት ዘመን ወጪ ትንተናን እና የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ከግምት ያስገባ ዘላቂነት ያለው የግዥ አፈፃፀም አሰራርን በፍላጎት መግለጫ፣ በመገምገሚያ መስፈርት፣ በውል ቃላትና ሐረጎች ዝግጅት ወቅት፣ እንዲሁም በውል አፈፃፀም ቁጥጥር ወቅት ተግባራዊ መደረግ እንዳለባቸው ያብራራል፡፡

በተመሳሳይ ይህን አዋጅ ለማስፈጸም በወጣው የፌዴራል መንግስት የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017 ክፍል ሰባት ላይ ዘላቂነት ያለው የግዥ ስርዓትን ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በተለይም ግዥው የህይወት ዘመን ወጪ ትንተና የሚሰራለት፣ የአካባቢ ጥበቃን ታሳቢ ያደረገ እና የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት ያብራራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለስልጣኑ አዋጁንና መመሪያውን ሳይሸራረፍ መፈጸም ይቻል ዘንድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ከመስጠት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡