Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

News

በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከሁሉም የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች ጋር ውይይት ተካሄደ።

(ሰኔ 17/2017 ዓ.ም)፣ የፌዴራል የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከሁሉም የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች እና የግዥና ንብረት ኃላፊዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ዙሪያ በጋራ ለመገምገም እና የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድን የጋራ ለማድረግ በማለም የተዘጋጀ መድረክ ነው ።

የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱ በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የቀረበ ሲሆን በሪፖርቱ  በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ አበይት የሪፎርም ስራዎች፣ አዲሱን አዋጅ 1333/2016 ተከትሎ የወጡ የህግ ማዕቀፍ ዝግጅትና ማሻሻያ ሥራዎችና የተካተቱ መሠረታዊ ለውጦች፣ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱን ወደ ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ከማውረድ ጋር የተያያዙ ተግባራት፣ የተዘጋጁና ጸድቀው ተግባር ላይ የዋሉ መመሪያዎች፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ጥራትና ቅልጥፍናን ለመጨመር የተተገበሩ የዲጅታል ስራዎች በተለይም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (ኢጅፒ) ትግበራን ይበልጥ ለማሳለጥ የተሻሻሉ ትግበራዎችና የሲስተሙ ጠቀሜታዎችና አዋጭነት ፣ የቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች፣ የተሠጡ ስልጠናዎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎችና የተገኙ ውጤቶች በስፋት ተተንትነው ቀርበዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘውም የ2018 በጀት ዓመት እቅድን ያቀረቡ ሲሆን እቅዱ የ2017  በጀት ዓመት ክንውንን መነሻ ያደረገና የተገኙ መልካም ውጤቶችን የምናስቀጥልበት በሌላ በኩል የነበሩብንን ክፍተቶች የምንሞላበት እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በተጨማሪም በኢ.ጂ.ፒ ሲስተም ትግበራ ዙሪያ የተደረጉ ማሻሻያዎች በአቶ እውነቱ አበራ (የኢ.ጂ.ፒ. ሲስተም አልሚና የፔራጎ ሥራ አሰኪያጅ ) የቀረበ ሲሆን ፣ በውስጥ አቅም ለምተው ስራ ላይ የዋሉ ዲጂታል ስራዎች (website, e- learning, letter management, …) በኢጂፒ ፕሮጀክት የአፕሊኬሽን ቲም ባለሞያ አቶ ኃይለሚካኤል ገብሩ አማካኝነት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በመጨረሻም የቀረቡትን ገለፃዎችን መነሻ በማድረግ ከመድረክ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ምላሽና ተቋማዊ የማጠቃለያ እና የቀጣይ የጋራ ስራ አቅጣጫዎችና የባለስልጣኑን የመተግበር ዝግጁነት በመግለጽ የዕለቱ መርሃ-ግብር ተጠናቋል።

በ2017 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀምና በ2018 በጀት ዓመት እቅድ ዙሪያ ውይይት ተካሄደ።


(ሰኔ 13/2017 ዓ.ም)፣ የፌዴራል የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን አመራርና ሰራተኞች የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀማቸውን በጋራ ገምግመዋል።

የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱ በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የቀረበ ሲሆን በሪፖርቱ  በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ አበይት የሪፎርም ስራዎች፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ጥራትና ቅልጥፍናን ለመጨመር የተተገበሩ የዲጅታል ስራዎች፣ ቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች፣ የሰው ሀይል ግንባታ ላይ የተከናወኑ አበይት ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎችና የተገኙ ውጤቶች በስፋት ተተንትነው ቀርበዋል።

ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘውም የ2018 በጀት ዓመት እቅድን ያቀረቡ ሲሆን እቅዱ የ2017  በጀት ዓመት ክንውንን መነሻ ያደረገና የተገኙ መልካም ውጤቶችን የምናስቀጥልበት በሌላ በኩል የነበሩብንን ክፍተቶች የምንሞላበት እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጄ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በተጨማሪም በውስጥ አቅም ለምተው ስራ ላይ የዋሉ ዲጂታል ስራዎች (website, e- learning, letter management, …) በኢጂፒ ፕሮጀክት ባለሞያዎች አማካኝነት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በመጨረሻም የቀረቡትን ገለፃዎች መነሻ በማድረግ ከመድረክ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በክብርት ወ/ሮ መሰረት የማጠቃለያ እና የቀጣይ ስራ አቅጣጫ የዕለቱ መርሃ-ግብር ተጠናቋል።

የሴት ሰራተኞች የፎረም አመራርና አባላት የውይይት መድረክ አካሄዱ፡፡

(ሰኔ 7/2017) በቢሾፍቱ ከተማ ፒራሚድ ሆቴል በተዘጋጀው መድረክ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ሴት ሠራተኞች ፎረም አመራር እና አባላት በፎረሙ ህገ-ደንብና በቀሪ ወራት ዕቅድ ዙሪያ ተወያይተው ለተፈጻሚነት ለማጽደቅ ያለመ መድረክ ነው፡፡

በመድረኩ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌን ጨምሮ ሁሉም ሴት ሰራተኞች እና የፎረሙ ተባባሪ አባል የሆኑ ወንድ ሠራተኞች የተሳተፉ ሲሆን የፎረሙን የመመስረቻ ህገ-ደንብ እና የቀሪ ወራት ዕቅድ ለአባላት ቀርበው እና ተወያይተውበት ለግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡

የተነሱ ሁሉም ግብዓቶች ተካተውበት የተቋቋመበትንም ዓላማ ለማሳካት የሚመጥን ህገ-ደንብ ተዘጋጅቶለት ለአፈጻጸም በሚያመች መልኩ ህገ-ደንብ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ ለተነሱ ሃሳቦች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶበት እንደሚሻሻል የጋራ ስምምነት ተደርሶበት ህገደንቡም እቅዱም በሙሉ ድምጽ ጸድቋል፡፡

በመጨረሻም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በንግግራቸው ፎረሙ ሴቶች እርስ በእርስ የሚመካከሩበት፤ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት የሚያጋጥማቸውን እንቅፋቶችም በግልጽ የሚነጋገሩበት ብሎም ነጻ ጊዜ የሚያገኙበት እና ማህበራዊ ግንኙነታቸውን የሚያዳብሩበት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው እና እንደ ተቋምም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዕድል የሚሰጥ ትልቅ ሚናን የሚጫወት በመሆኑ ተቋሙ ሴት ተኮር ስልጠናዎችን፣ተጨማሪ ገቢ ማስገኛ ስራዎችን ለዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሠራተኞች ከሚመለከታቸው አደረጃጀቶች ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ማመቻቸት እና ቅድመ ስልጠናዎችን ማዘጋጀት፤በጥቅሉ ሴቶች በስነ-ልቦና፤በኢኮኖሚ፤በፈጠራ ችሎታቸው የተሻሉ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ የትኛውንም ተቋማዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ዋና ዳይሬክተሯ በአስተሳሳብ እና በአመራር ብቃት የተለወጡ መሪዎችን ለማፍራት አጋዥ የሆነውን በሣይንሳዊ ጥናት ተደግፎ አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው የስራ አመራር እና መሪነት መካከል ያለውን ልዩነት እንዲሁም የመሪነት አስፈላጊነት፤ታሪካዊ የዕድገት ደረጃዎች፤ዘይቤና ክህሎቶች፤ዋና ዋና ተግባራትና መርሆች እንዲሁም ዘመናዊ የአመራር አስተሳሰቦች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ገለጻ ተሰጥቶበታል፡፡

በመጨረሻም ተሳታፊዎች በቀረበው ስልጠና ዙሪያ ሃሳብ አስተያየቶችን በሰፊው በመስጠት የዕለቱን መረሃ- ግብር በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡

በኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዥ ሥርዓት ዙሪያ ከባንኮች እና ኢንሹራንሶች ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡

(ሰኔ 5/2017 ዓ/ም) ባለስልጣኑ በኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዥ ሥርዓት ዙሪያ በርካታ ተግባራትን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትስስር ተግባራዊ እያደረገ እና አሰራሩን ይበልጥ እያዘመነ ለዲጅታል ኢኮኖሚ ዘርፉ ሃገራዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል፡፡

ይህንን ተከትሎ ከባንኮች እና ኢንሹራንሶች ጋር በጋራ መስራት የሚገባ ተግባር በመሆኑ ቀደም ሲል ሲስተሙን አስተሳስሮ ለመተግበር ባለስልጣኑ መድረክ የፈጠረ ቢሆንም ተግባራዊነቱ ተጠናክሮ ባለመቀጠሉ ዳግም ተወያይቶ ለትስስሩ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ በካፒታል ሆቴል የተዘጋጀ መድረክ ነው፡፡

መድረኩን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የከፈቱ ሲሆን ከመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ጋር ተያያዥ ገለጻ በመስጠት የግዥ ስርዓቱ የደረሰበትን አጠቃላይ ሁኔታ፣ ያስገኛቸው ጠቀሜታዎች፤በትግበራ ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና አስቻይ ሁኔታዎችን በገላጻቸዉ ወቅት አካተዋል፡፡

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን የገለጻቸው አካል ያደረጉት ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ ረገድ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ግንባር ቀደም ሚና ከሚጫወቱ ተቋማት መካከል መሆናቸውን አስታውሰው የዲጅታል ሽግግር ጉዞ ማሳያ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን የኤሌክትሮኒክ ግዥ አፈጻጸም ሥርዓትን በመተግበር ሂደት የሲስተም ትስስር ሊፈጥሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በመቀጠልም በግዥ ሂደት ሲስተሙ የሚያተናግዳቸው ትግባራዎች በዝርዝር በማመላከት ከነዚህም መካከል መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል፤ከአቅራቢዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው ተቋማት ጋር የሲስተም ትስስር መደረጉን አስታውሰው በቀጣይ በኢጂፒ ሲስተም በኩል ብቻ ግዥ መፈጸም እንዳለበት የሚደነግገው ህግ ተፈጻሚነት በማረጋገጥ በመንግስት ግዥ ላይ የሚስተዋለውን የውስንነት ችግር ለመፍታት እና ከእጂ ንክኪ የጸዳ ለማድረግ ብሎም ደህንነቱ የተጠበቀ የደንበኞችን እርካታ የሚያረጋግጥ የዘመነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ተገቢ ስለሆነ በትስሰር ሊተገበር እንደሚገባ ገልጸው ስርዓቱን ተጠቅመው ባንኮች እና ኢንሹራንሶች የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በግልጽ ተገንዝበው በሲስተሙ መተግበር እንደሚገባቸው አብራርተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተራ በገለጻቸው በዚሁ የግዥ ስርዓት በርካታ የገንዘብ ቁጥር ያለዉ ግዥ የሚፈጸም እና በሂደቱም ዋስትና የሚጠየቅባቸው በሲስተሙ በፈሰሱ ጨረታዎች ልክ የሚሆንበት አሰራር በወረቀት ሊተገበር ስለማይገባ አስተማመኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ዋስትና በሲስተም ሊታሰርለት ይገባል ብለዋል፡፡ ባንኮችና ኢንሹራንሶችም መሰል ጉዳዩችን በበይነ በርብ አለማድረጋቸው የተፈለገውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንቅፍት ስለሆነ ይህን ተፈጻሚ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ሂደቶች ሳይዛነፉ እንዲተገበሩ ለማድረግ ውይይቱ ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም የሲስተም ትስስሩ በባንኮች እና ኢንሹራንሶች እንዴት ተፈጻሚ እንደሚሆን የሲስተሙን ሂደት በግልጽ ያመላከተ ገለጻ በቪዲዩ በማስደገፍ በአልሚው ድርጅት/ፔራጎ/ ከፍተኛ ባለሙያ በአቶ ኤልያስ ጥበቡ አማካኝነት ለተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡

የቀረበውን የውይይት መነሻ ሃሳብ መሰረት በማድረግ ተሳታፊዎች አስተያየት የሰጡ ሲሆን ባለስልጠኑ የግዥ ስርዓቱን ለማዘመን የሄደበትን እርቀት አድንቀው የሲስተም ትስስሩን በተመለከተ በአዎንታዊ ጎኑ የተቀበሉት እና ለመተግበርም ዝግጁነታቸውን የገለጹ ሲሆን ተገቢውን ቴክኒካል ስልጠና ከማግኘት አንጻር፤ከደንበኞቻቸው የአገልግሎት መስጫ ማዕከል እና ሌሎች ቴክኒካል ጉዳዩች ጋር የተያያዙ ሃሳቦችን ምላሽ በሚሹት ጎራ አንስተዋል፡፡

ለተነሱ ሃሳቦች ተቋማዊ ምላሽ የሰጡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መስረት መስቀሌ በማጠቃለያቸዉ የመድረኩ ተሳታፊ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ትስስር ለመፍጠር ላሳዩት ፈቃደኝነት ልባዊ ምስጋናቸውን በመቸር በቀጣይ የስራ ውል ስምምነት በመፈራረም ወደ ትግበራ የሚገባ እና ፈጥነው ተግባራዊ የሚያደርጉ ባንኮችን እውቅና በመስጠት በሚዲያ ጭምር ለህዝብ ተደራሽ የሚሆንበት አሰራር እንደሚኖር አስታውሰው ፈጥኖ መተግበር ያለበት ጉዳይ በመሆኑ ባለስልጣኑ ባለሙያ በመመደብ በስፍራው አልያም በማዕከል ደረጃ ስልጠና ሰጥቶ በአጭር ቀናት ውስጥ ወደ ትግበራ እንደሚያስገባ እና ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በአሰራሩ ከ2018 በጀት ዓመት ጀምሮ የማንዋል መረጃ የማንቀበል በመሆኑ ማንኛውም ግዥ ፈጻሚ መ/ቤት የማንዋል ዋስትናን የማይቀበልበት አሰራር ይዘረጋል ፣ በሂደትም አስገዳጅ ሆኖ ሲስተሙ ራሱ የሚዘጋበት ሂደትን በማካተት የሚተገበር በመሆኑ ይህንን ተገንዝበን ለተግባራዊነቱ ዝግጁ ልንሆን ይገባል በማለት የውይይቱን መርሃ-ግብር አጠናቅቀዋል፡፡