Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

News

የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት በግዥ ሂደት ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ነው፦ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን

(መስከረም 08/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) በሚተገበርበት ሁኔታ ላይ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ወቅት ባለስልጣኑ የግዥ ሂድቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ አብራርተዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ ተደራሽነትን በማስፋት፣ አሳታፊነትን በመጨመር፣ ወጪን በመቀነስ እና ግልጸኝነትን በማስፈን በኩል ያለው አስተዋጽዖ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው ሁሉም የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ግዣቸውን በዚህ ስርዓት እየፈጸሙ የሚገኙ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ስድስት ክልሎች ወደ ትገበራ እየገቡ እንደሚገኙ እንዲሁም ሌሎች ክልሎችም ስርዓቱን እንዲተገብሩት ለማስቻል ተከታታይ ውይይቶች እየተደረገና ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ስርዓት በግዥ ሂደት ውስጥ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ስርዓት ነው ሲሉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገልጸዋል። ‎

‎የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን መንግሥት በተቋማት ሪፎርም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው በግዥ ስርዓቱ እየተደረገ ያለው ሪፎርም አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘውም ‎የግዥ ስርዓቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ በግዥ ሂደት ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን የክልሉ መንግሥት የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኑንና ለዚሁ የሚያግዝ አዋጅ መጽደቁን አመላክተዋል።

በመጨረሻም ስርዓቱን ተግብሮ ለማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠባቸው ሲሆን ክልሉ ወደ ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት ለመግባት በሚያደረገው ጥረት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ድጋፉን እንዲያጠናክርም ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል።

ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት ተደረገ።

(መስከረም 06/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአሰራር ስርዓቱን በማዘመንና ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየስራ የሚገኝ ሲሆን አዋጅ ከማሻሻል ጀምሮ የተለያዩ መመሪያዎችንና የአሰራር ማኑዋሎቸነ በማዘጋጀት ወደ ስራ ገብቷል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለውጡን ለማስቀጠልና የጋራ ለማድረግ እየተገበራቸው የሚገኙ ተግባራትን ለተገልጋዩ ማህበረሰብና ለባለድርሻ አካላትም እያሳወቀ ይገኛል። በዚሀም ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች እና ከሸሪዓ ፍርድ ቤት ከፍተኛ አመራሮች እና ዳኞች ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ላይ በፌዴራል ግዥና ንብረት ባለስልጣን እየተተገበሩ የሚገኙ አበይት የለውጥ ተግባራት በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ለውይይት ቀርቧል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰፋፊ የለውጥ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን አዋጅ 1333/2016፣ የግዥ አፈጻጻም መመሪያ 1073/2017፣ የመድሐኒትና ህክምና መሳሪያዎች የግዥ መመሪያ ቁጥር1066/2017፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ግዥ መመሪያ 1070/2017፣ የንብረትና ተሽከርካሪ አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1095/2017 ወጥተው መተግበራቸውን አመላክተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ አዋጅን በብሬል  ማሳተም፣ የስነ-ምግባር መመሪያ ማዘጋጀትና መተግበር፣ የተገልጋይ ቻርተር ማዘጋጀትና ተግባር ላይ ማዋል እና ሌሎች የለውጥ ተግባራት ተተንትነዋል።  

በሌላ በኩል በፌዴራል የመንግስት ግዥ አፈጻጸም መመሪያ ላይ በባለስልጣኑ የግዥ ማሻሻያ እና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ተጓዴ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በክብርት ዋና ዳይሬክተሯ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው መርሃ- ግብሩ ፍጻሜውን አግኝቷል።

በፌዴራል መንግስት የተያዙ የልማት ድርጅቶች የግዥ መመሪያ 1070/2017 ላይ ስልጠና እና የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።

(ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በፌዴራል መንግስት ከተያዙ የልማት ድርጅቶች ጋር የግዥ አፈጻጸም እና የንብረት አያያዝን በሚመለከት ውይይት እያደረገ ይገኛል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአሰራር ስርዓቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ ቀልጣፋ፣ ታዓማኒ፣ አካታች እና ጥራት ያለው ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን የግዥ አዋጁን ከማሻሻል ጀምሮ የፌዴራል ግዥ መመሪያን፣ የፌዴራል ንብረት መመሪያን፣ በፌዴራል መንግስት ባለቤትነት የተያዙ የልማት ድርጅቶች ግዥ መመሪያን እና የመድሐኒትና የህክምና ቁሳቁሶች መመሪያን በማውጣት ስራ ላይ እንዲውሉ አድርጓል።

በአዋጅ 1333/2016 ከተካተቱ አበይት ተግባራት አንዱ በፌዴራል መንግስት የተያዙ የልማት ድርጅቶች ግዛቸውን በኤሌክትሮኒክ ስርዓት እንዲፈጽሙ የሚያስችል ሲሆን የግዥ መመሪያውም የስራ ባህሪያቸውን መሰረት ያደረግ እንዲሆን የማድረግ ስራ ተሰርቷል።

ይህን ተከትሎም የልማት ድርጅቶች ውጤታማ የግዥና ንብረት አስተዳደር ስርዓት ሊገነቡ በሚችሉበት እና መመሪያውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊፈጽሙ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።

የውይይት መነሻ ጽሁፍ እና በ2017 በጀት ዓመት የተተገበሩ አበይት ክንውኖችን ለውይይት ያቀረቡት የግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ውጤታማ የግዥ እቅድ ለውጤታማ ስራ ክንውን መሰረት መሆኑን ያብራሩ ሲሆን ግዥ ያለ እቅድ መፈጸም እንደሌልበትም አብራርተዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ አካታችነትን በማስፈን፣ ግልጽ የአሰራር ስርዓትን በመፈጠር፣ የተሳታፊን ቁጥር በመጨመር፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው የግዥ ሂደትን እውን በማድረግ በኩል ችግር ፈቺ ስርዓት መሆኑን አመላክተዋል።

የክብርት ወ/ሮ መሰረትን ገለጻ ተከትሎ በፌዴራል መንግስት ባለቤትነት የተያዙ የልማት ድርጅቶች የግዥ መመሪያ 1070/2017 ላይ በአቶ ገብያው ይታይህ እና በወ/ሮ አየናቸው ቸርነት ስልጠና እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን ስልጠናውም ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።

በአገልግሎት አስተዳደር ሪፎርም የተግባር ምዕራፍ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሄደ።

(ነሐሴ 25/2017 ዓ/ም)፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በ2017 በጀት ዓመት የለውጥ ዝግጅት ምዕራፍን በተሳካ ሁኔታ ማከናወኑን ተከትሎ በአገልግሎትና አስተዳደር የተግባር ምዕራፍ ዕቅድ ዙሪያ ከአምራሩና ከሰራተኞች ጋር ውይይት አድርጓል።

ውይይቱ ተቋማዊ ባህልን መገንባት እና የትግበራ ምዕራፉን በተሳካ ሁኔታን ለመወጣት ያለመ ሲሆን ቅንጅታዊ አሰራርን አጠናክሮ በተነሳሽነት እና በአንድ ዓላማ ወደ ትግበራ መግባት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።

በውይይቱ በአገልግሎትና በአስተዳደር ሪፎርም የተሰሩ አበይት ስራዎችና በትግበራ ምዕራፉ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ተግባራት በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ቀርቦ ውይይት ተደርጐበታል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው በሪፎርም ስራው የአመራሩ እና የሰራተኛው ተነሳሽነት፣ ተግባራትን ለመፈጸም የነበረ ቅንነት፣ ቁርጠኝነትና ተግባቦት እጅግ የሚያስመሰግን የነበረ ሲሆን ውጤቱም የሁሉም አመራርና ሰራተኛ ልፋት፣ ጥረትና ድካም ውጤት ነው በማለት ገልፀዋል።

አያይዘውም በሪፎርም የእቅድ ምዕራፉ ላይ ከ21 መመሪያዎች እና የአሰራር ስርዓቶች መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል። በተለይም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ስራዎችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ስራ መሰራቱ የተገለጸ ሲሆን በዚህም ኤሌክትሮኒክስ የመንግስት ግዥ (e-GP) ላይ ከ29,340 አቅራቢዎች መመዝገባቸው፣ ሁሉም የፌዴራል ተቋማት ግዣቸውን በኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) መፈፀም መቻላቸው እንዲሁም በተሽከርካሪ ስምሪትና ቁጥጥር ስርዓት (e- Fleet Management)፣ ቅሬታ እና ጥቆማ መቀበያን ዲጂታላይ በማድረግ፣ በኤሌክትሮኒክ ትምህርት (e-Learning)፣ ዲጂታል ደብዳቤ (e- Lettering) ስርዓቶች ውጤታማ ሆነው እየተተገበሩ መሆናቸው ተጠቅሷ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቀጣይ የትግበራ ምዕራፍ ላይ አስተዳደርና አደረጃጀት፣ ዘመናዊ የሰራተኞች መረጃ አያያዝ፣ ፍትሐዊና ተደራሽ የመንግስት ግዥ፣ ዲጂታል የመንግስት ግዥ፣ ብዝሃነትና አካታችነት፣ የሰራተኞች ብቃትና ምዘና ማረጋገጥ በሚቻልበተ ሁኒታ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተብራርቷል።

የክብርት ዋና ዳይሬክትሯን ገለጻ ተከትሎ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በዋና ዳይሬክተሯ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በመጨረሻም በ2017 በጀት ዓመት ከፍተኛ አፈጻጸም ላስመዘገቡ አመራሮች፣ ስራ ክፍሎች እና ሰራተኞች የእውቅና እና የምስጋና የምስክረ ወረቀት በማበርከት የዕለቱ መርሃግብር ተጠናቋል።